
አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ህፃናትን ለጦርነት በማሰለፍ የሚፈፅመውን ወንጀል ለማውገዝ ዓለም አቀፍ የትዊተር ዘመቻ ተጀመረ።
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 09/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው የትህነግ ቡድን ህፃናትን ለጦርነት በማሰለፍ የሚፈፅመውን ወንጀል ለማውገዝና ተጠያቂ እንዲሆን የሚጠይቅ ዓለም አቀፍ የትዊተር ዘመቻ እየተካሄደ ነው።
በመላው ዓለም የሚገኙ የትዊተር ማኅበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ የሆኑ ኢትዮጵያዊንና የኢትዮጵያ ወዳጆች እንዲሁም ዳያስፖራዎች የአሸባሪውን የሕወሃት ቡድን ድርጊት በመቃዎም ነው ዘመቻውን እያደረጉ ያሉት።
ቡድኑ በትግራይ ክልል እያደረሰ ያለውን የሰብዓዊ መብት ጥሰትና ህፃናት ለጦርነት ማሰለፉን በተመለከተ ለዓለም ማህበረሰብ ለማሳወቅ እና ድርጊቱን በይፋ ለማውገዝ የተጀመረ የትዊተር ዘመቻ ነው።
ቡድኑ ህፃናትን አደንዛዥ ዕፅ በማስጠቀም ወደ ጦር ግንባር እንዲሰለፉ እያደረገ ያለበት ሁኔታ የአለም አቀፉን የህፃናት መብት የሚጣረስ የጦር ወንጀል ነው የሚል መዕልክት ትዊት እያደረጉ ነው።
የአለም አቀፉ ማኅበረሰብ፣ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑ የኢትዮጵያ ወዳጆች እዲሁም አለም አቀፍ ተቋማት ሕወሓት በሕፃናት ላይ እያደረሰ ያለውን ድርጊት እንዲያወግዘ ጥሪ አቅርበዋል።
አንዳንድ የዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኀን አሸባሪው ቡድን ህፃናትን ለጦርነት በማሰለፍ እያደረገ ያለውን ድርጊት ለማስተባበል መሞከራቸው እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትሕ ኢዜማ መሪ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ሕወሓት ሕጻናትን ለውጊያ እየመለመለና እያሰማራ እንደሚገኝ በርካታ ዘገባዎች እየወጡ እንደሚገኝ በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት አስተያየት ገልጸዋል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) የሕዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ጣሒር መሐመድ “ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለትግራይ ሕዝብ ተጨንቀናል በማለት ሀሳቡን ሲገልጹ የቆዩ ቢሆንም፤ በወታደራዊ ግጭት አሸባሪው ሕወሓት ሕጻናትን ለውትድርና ሲጠቀም ዝምታን መርጠዋል” ብለዋል።
ሕወሓት እየፈጸመ ያለው ድርጊትም የጦር ወንጀል መሆኑን ነው የገለጹት።
የሴቶች ሕጻናትና ወጣቶች ሚኒስቴር የእናቶችና ሕጻናት ጤና እና የስርዓተ ምግብ ዳይሬክተር ዶክተር መሰረት ዘላለም፤ ሕጻናትን በጦርነት ውስጥ ማሳተፍ የጦር ወንጀል ነው፤ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሕጻናት መብት ኮንቬንሽን የጣሰ ነው ብለዋል።
ሁሉም በዚህ ጉዳይ ላይ ምንም አይነት ትዕግስት ሊኖረው እንደማይገባ ገልጸዋል።
#childernnotsoldiers #TPLFterriorist #ChildSoliders #actofevil #warcrime #ACTtoprotect የሚል መልዕክት የያዙ የትዊተር ሀሽታጎች መልዕክቶች በመተላለፍ ላይ ይገኛሉ።
በተጨማሪም #Ethiopia #UnityForEthiopia #GERD #FillTTheDam፣ #International #SaveEritreanRefugeesInTigray በሚሉ ሀሽታጎች በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ መልዕክቶች እየተሰራጩ ይገኛሉ።
ይህ ዘገባ እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ #childernnotsoldiers የሚለው ሀሽታግ ከ100 ሺህ ጊዜ በላይ ትዊት የተደረገ ሲሆን እና #Ethiopia ሀሽታግ ከ161 ሺህ ጊዜ በላይ ትዊት ተደርጓል።
እ.አ.አ በ1989 የጸደቀው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሕጻናት መብቶች ኮንቬንሸን አንቀጽ 38 ንዑስ አንቀጽ 3 የትኛውም አካል ሕጻናትን በውጊያ ውስጥ ወታደር አድርጎ መመልመል እንደሌላባቸው የሚገልጽ ሲሆን፤ ድርጊቱ በሕግ የተከለከለ መሆኑን ያስቀምጣል። ኢዜአ እንደዘገበው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ