
“የክልሉ መንግሥት ያደረገው ጥሪ የምንወዳትን ሀገር በድጋሜ ለማገልገል ዕድል ፈጥሮልናል” በደባርቅ ከተማ የሚገኙ የቀድሞ የመከላከያ ሠራዊት አባላት
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 09/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአሸባሪው ትህነግ ቡድን በከፈተው ጥቃት የአማራን ብሎም የኢትዮጵያን ሕዝብ ለህልውና አደጋ በማጋለጡ ምክንያት የክልሉ መንግሥት ለሕዝቡና ለቀድሞ የመከላከያ አባላት በሙሉ ጥሪ ማስተላለፉ ይታወሳል፡፡
በደባርቅ ከተማ በርካታ የቀድሞ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ጥሪውን ተቀብለው ወደ ተሰጣቸው ግዳጅ ለመሄድ ዝግጁ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡ የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽንም በደባርቅ ከተማ ጥሪውን የተቀበሉ የቀድሞ የመከላከያ ሠራዊት አባላትን ሲመዘገቡ በቦታው ተገኝቶ አነጋግሯል፡፡
ጥሪውን ከተቀበሉት መካከል ሻምበል ባሻ አሻግሬ ሀገሪቱ ከምንጊዜውም በላይ ችግር ላይ ትገኛለች ብለዋል፡፡ ችግር እየፈጠሩ ያሉት ደግሞ የትህነግ ጁንታዎች ናቸው፤ እነዚህን አጥፊዎች የማጥፋትና ኢትዮጵያን ከችግር የማውጣት ኀላፊነት ስላለብን ጥሪውን ተቀብለን የምንወደውን ሕዝብ ለማገልገል ወደ ቀድሞ ሥራችን ተመልሰናል ብለዋል፡፡
ድሮውንም አሸባሪው ትህነግ ከመከላከያ ሠራዊት አገልግሎት ውጭ ያደረገን አማራ በመኾናችንና ለአማራ ሕዝብ የመረረ ጥላቻ ስላለው ነው ያሉት ደግሞ ሸጋው ሙሉዬ ናቸው፡፡ የአየር ኀይል ጥገና ባለሙያ እንደነበሩና በግፍ ከሙያ ውጪ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡ ወጣቱን በሙያው በማሰልጠንና በግንባር ጁንታውን በመዋጋት የኢትዮጵያ ሕዝብ በሰላም ወጥቶ እንዲገባ ለማድረግ ጥሪውን መቀበላቸውን ገልጸዋል፡፡
ሌላኛው ጥሪውን የተቀበሉት የቀድም መከላከያ ሠራዊት አስር አለቃ ሙሉጌታ የመከላከያ ሠራዊት የኮማንዶ አሰልጣኝ የነበረና በትህነግ በግፍ ከሙያው የተባረረ ወጣት ነው፡፡ ትህነግ በአማራ ሕዝብ ላይ ሂሳብ የማወራረድ፣ ኢትዮጵያንም የመበተን አቅም የለውም የሚለው አስር አለቃ ሙሉ ጌታ ዓላማው ሀገር ጫና ውስጥ እንድትገባና ሕዝብን ሰላም መንሳት ነው ብሏል፡፡
የክልሉ መንግሥት ያደረገው ጥሪ ይህን ኀይል ለማስወገድና ሀገርን ዳግም በሙያ ለማገልገል እድል መፍጠሩን ነው የነገረን፡፡ ወጣቱን በማሰልጠንም ኾነ በውጊያ አውድ በመሳተፍ ጁንታውን ለመደምሰስ ዝግጁ እንደኾነም አረጋግጧል፡፡
የቀድሞ መከላከያ ሠራዊት አባላት በክልሉ መንግሥት የተደረገው ጥሪ እንዳስደሰታቸውና ጥሪውን ለመቀበል ወደኀላ እንዳላሉም ተናግረዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አድኖ ማርቆስ – ከደባርቅ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ