“…እኛ የታጠቀውንም ያልታጠቀውንም ካልመራን እና በየደረጃችን መውሰድ የሚገባንን ኀላፊነት ካልወሰድን ሕዝቡ የሕልውና አደጋ ውስጥ ይወድቃል” ኮሎኔል ማርዬ በየነ

311
“…እኛ የታጠቀውንም ያልታጠቀውንም ካልመራን እና በየደረጃችን መውሰድ የሚገባንን ኀላፊነት ካልወሰድን ሕዝቡ የሕልውና አደጋ ውስጥ ይወድቃል” ኮሎኔል ማርዬ በየነ
ባሕር ዳር: ሐምሌ 09/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የልጅነት፣ የወጣትነት እና የጎልማሳነት እድሜዬን ያሳለፍኩት በሀገር መከላከያ ሠራዊት ውስጥ ነው ብለዋል፡፡ ስለ እናት ሀገር ኢትዮጵያ 31 ዓመታት በዱር፣ በገደል፣ በነዳድ በረሃ በጠረፍ አሳልፈዋል፤ ኢትዮጵያ ቋንቋቸው፣ ሕይወታቸው፣ ኑሯቸው፣ መመኪያቸው እና መኩሪያቸው ናት፡፡
ኢትዮጵያ የሰጠቻቸውን ኀላፊነት በጸና እምነትና በማይፈታ ጀግንነት በአግባቡ ተወጥተዋል፡፡ ከእግረኛ ጦረኛ ጀምረው በልዩ ልዩ ኀላፊነት ሀገራቸውን አገልግለዋል፡፡ እድሜና ሕይወታቸውን ሰጥተዋል፤ ከ31 ዓመታት በኋላ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ሲወጡም የአሸባሪው ትህነግ ጄኔራሎች ሴራ እና የእሳቸው የጸና ኢትዮጵያዊነት ባለመጣጣሙ ነበር፡፡ አሸባሪው ትህነግ የአማራ ጠልነቱና በኢትዮጵያዊነት ያለው አቋም ስላልጣማቸው ከሚወዱትና ከኖሩበት ሙያ ወጥተዋል፡፡
ታዲያ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ይውጡ እንጂ ሕዝብና ሀገርን ከሚታደግ ኃይል አልራቁም፡፡ የአማራ ልዩ ኃይልን በመደገፍና በማደራጀት ከፍተኛ አስተዋጽዖ አድርገዋል፡፡ በሙያቸው ድጋፍ በማድረግም ከጸጥታ ተቋሙ አይርቁም፡፡ አሁን ላይም የአማራ ክልል መንግሥት ያቀረበውን ጥሪ ተቀብለው ትግሉን ተቀላቅለዋል ኮሎኔል ማርዬ በየነ፡፡
ኮሎኔሉ ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር በነበራቸው ቆይታ የአሸባሪውን ትህነግ ሴራና ተንኮል በነበራቸው የትግል ወቅት ጠንቅቀው እንደሚያውቁት ነው የተናገሩት፡፡ አሸባሪው ትህነግ ለኢትዮጵያ ሊሠሩ የሚችሉ፣ ለኢትዮጵያዊነት የሚቆረቆሩ እና ታላላቅ ሰዎችን አስቀድሞ መግደሉንም ገልጸዋል፡፡
የአሸባሪው ትህነግ አካሄድ እና ተንኮል አሁን የተጀመረ አለመሆኑንም ነው የተናገሩት፡፡ የሽብር ቡድኑ የአማራ ጠልነት አሁን ላይ የተጀመረ አይደለም፤ የቆዬ ነውም ብለዋል፡፡
የአማራ ሕዝብ፣ መንግሥትና ሌሎች አካላት በጋራ ከተባበሩ ርዝራዦቹን ለመጠራረግ ጊዜ አይወስድም ነው ያሉት፡፡
የአማራ ክልልን የጸጥታ ኃይል ማጠናከር ወሳኙ ነገር መሆኑንም ገልጸዋል፡፡ የክልሉ መንግሥት ጥሪ ያደረገለት ኃይል የጸጥታ መዋቅሩን ሲቀላቀል የሚፈጥረው አቅም ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡
ኮሎኔል ማርዬ የክልሉ መንግሥት የወሰደው የሕልውና ዘመቻ የሚደገፍ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ጥሪ የተደረገላቸው የጦር መኮንኖች እየገቡ መሆናቸውን የገለጹት ኮሎኔል ማርዬ “እኛ ካልገባን፣ እኛ ካልታደግነው፣ እኛ የታጠቀውንም ያልታጠቀውንም ካልመራነውና በየደረጃችን መውሰድ የሚገባንን ኀላፊነት ካልወሰድን ሕዝቡ የሕልውና አደጋ ውስጥ ይወድቃል” ነው ያሉት፡፡
አሸባሪውን ትህነግ ለመደምሰስ የሚደረገው የህልውና ዘመቻ የአማራ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያ ስለመሆኑም ኮሎኔል ማርዬ ገልጸዋል፡፡
አሸባሪው ትህነግ ኢትዮጵያውያንን ለማባላት እድል እንዳያገኝ ማድረግ ከሁሉም ኢትዮጵያዊ እንደሚጠበቅም መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
የሕዝቡ መልካም ምላሽና መደገጋፍ ትልቅ አቅም እየፈጠረ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
ሚሊሻው ለዘመቻ እየከተተ መሆኑን የተናገሩት ኮሌኔሉ የጸጥታ ኃይሉ ከፍተኛ የሥነ ልቦና ደረጃ ላይ ያለ ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡
ኮሎኔል ማርዬ የኢትዮጵያ ሕዝብ በአሸባሪው ትህነግ ላይ የመጀመሪያ እርምጃ ሲወሰድ እንዳሳየው አንድነት አሁንም ማሳዬት ይገባዋል ብለዋል፡፡ ምክንያቱም ርዝራዡን የማጽዳት ሥራው አልተጠናቀቀም ነው ያሉት፡፡ ጦርነት ለድል የሚበቃው ሕዝባዊ ድጋፍ ሲኖረው ነው ያሉት ኮሎኔሉ ኢትዮጵያውያን ከጫፍ እስከ ጫፍ ለመንግሥትና ለሠራዊቱ ድጋፍ ማድረግ አለባቸውም ብለዋል፡፡
በቂ የሰው ኃይልና አቅም አለን ያሉት ኮሎኔሉ ድጋፍ በማድረግ ሕዝቡ የድርሻውን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleሁሉም የብዙኃን መገናኛ ተቋማት የጋዜጠኝነት ሙያ ሥነ ምግባርን ተከትለው እንዲሠሩ የመገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን ጥሪ አቀረበ፡፡
Next articleበኩር ጋዜጣ ሐምሌ 12/2013 ዕትም