
“እንደ አንድ ልብ ሆነን የተደቀነብንን ሀገር የማፍረስ ተግባር መመከት ይገባናል” የሐረሪ ክልል
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 09/2013 ዓ.ም (አሚኮ) እንደ አንድ ልብ ሆነን የተደቀነብንን ሀገር የማፍረስ ተግባር መመከት ይገባናል ሲል የሐረሪ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ በወጣው የአቋም መግለጫ ገለጸ፡፡
የሐረሪ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ያወጣው መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡
የሐረሪ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት የክልሉን ሕዝብ በማቀናጀት በኢትዮጵያ ላይ የሚቃጣውን የውስጥና የውጪ ትንኮሳን ለማክሸፍ ዝግጁነቱን ይገልፃል፡፡
ወትሮም ቢሆን ለስልጣን እንጂ ለሀገርና ሕዝብ ግድ የሌለው አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ከለውጡ ጅማሮ አንስቶ ሀገሪቱን እንደሚያሻግር ተስፋ የጣሉበትን ሀገራዊ ለውጥ ለመቀልበስ አንዴ ከውስጥና ውጪ ሆነው የኢትዮጵያን ውድቀት ከሚመኙ አካላት ጋር በማበርና በማሰለፍ ሀገሪቱን ለመበታተን ሲንቀሳቀስ ቆይቷል።
የጁንታው ሙከራዎች ሁሉ አልሳካ ሲለው የሀገራችንን ምልክት የሉዓላዊነታችን ደጀን የአፍሪካውን መመኪያ በሆነው የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላትን ጭካኔ በተሞላበት መልኩ በማጥቃት ከሀዲነቱን ዳግም አስመሰከረ። ሆኖም መላው ኢትዮጵያውያን አንድ ሆነው ከሀገር መከላከያ እና ከክልል የጸጥታ አካላት ጋር በመሆን አይቀጡ ቅጣት ተቀጥቶ ጫካ ለመግባት ተገዶ እና በሕዝብ መሀል ተሰግስጎ በአልሞት ባይ ተጋዳይነት ሲፍጨረጨር ቆየ።
ሆኖም መንግሥት የክልሉ በሁኔታው የተጎዳው የክልሉ ህዝብ ሰብአዊ ድጋፍ በበቂ ደረጃ ተደራሽ እንዲሆን እና አርሶ አደሩም እርሻውን እንዲከውን ታሳቢ በማድረግ የተናጠል የተኩስ አቁም እርምጃ ለሕዝብ ጥሩ የጥሞና ጊዜ የፈጠረ መሆኑን አምኖ ሲደግፍ ቆይቷል፡፡ ሆኖም ግን ሕወኃት/ጁንታ ለሕዝብ ጥቅም ተብሎ ለተደረገዉ ጥሪ ወደ ጎን በመተው ሕዝብ ቦታ እንደሌለዉ ጦርነት በማወጅና ትንኮሳ በመፈፀም በግልፅ በማሳየት ዛሬም እንደ የጦርነት ነጋሪት እየጎሰመ ይገኛል።
ጁንታው በተባበሩት መንግሥታት የወጣዉን የሕጻናት መብት ድንጋጌ በመጣስ የነገ ሀገር ተረካቢ ሕጻናትን ለጦርነት በመማገድ ላይ ይገኛል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አዛውንቶችን፣ እናቶችንና የሐይማኖት አባቶችን በማሰለፍ በእልቂታቸዉ የጀግንነት አክሊል ለመድፋት ይሞክራል፡፡ በመሆኑም በተለይም በአሁኑ ወቅት መላው ኢትዮጵያውን ከመቼውም ጊዜ በላይ በአሸባሪው ቡድን በሚነዙ የሐሰት ፕሮፖጋንዳ ሳንወናበድ፤ ውስጣዊ አንድነታችንን በማጠናከር፤ እርስ በርስ በመመካከርና በመደጋገፍ፤ የተቃጣብንን ሀገራዊ ጥቃት በሕብረትና በአንድነት፤ እንደ አንድ ልብ ሆነን የተደቀነብንን ሀገር የማፍረስ ተግባር መመከት ይገባናል።
የክልላችን ሕዝብና መንግሥትም በሀገር ህልውና ላይ የተቃጣውን አደጋ ለመመከት እንደወትሮው ያልተቆጠበ ሁለንተናዊ ድጋፍ እንደሚያደር ያረጋግጣል።
ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ ሕብረት ታፍራና ተከብራ ትኖራለች!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!!
የሐረሪ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት
ሐምሌ 2013
ሐረር