በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ግንባታቸው ለዓመታት ተጓቶ የነበሩት የዓሳ ማቆያ እና ማከፋፈያ ጣቢዎችን ለማጠናቀቅ እየተሠራ ነው፡፡

185

ባሕር ዳር፡ መስከረም 12/2012 ዓ.ም (አብመድ) አምስት ዘመናዊ የዓሳ ማቆያ እና ማከፋፈያ ጣቢያዎች ከአራት ወራት በኋላ ሙሉ በሙሉ ሥራ እንደሚጀምሩ የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ አስታወቀ፡፡

የተከዜ የሰው ሠራሽ ሐይቅ በዓመት ከ10 ሺህ ቶን በላይ የዓሳ ምርት በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ብቻ ይገኝበታል፡፡ 18 ዓይነት የዓሳ ዝርያዎች ያለው ሐይቁ በ14 ማኅበራት ለተደራጁ ከሦስት ሺህ አምስት መቶ በላይ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉንም የብሔረሰብ አስተዳደሩ የዓሳ ሀብት ልማትና ጥበቃ ባለሙያ አቶ ዝናቡ ፈቃዱ ተናግረዋል፡፡

በየቀኑ የሚመረተው ዓሳም ለገበያ ሳይቀርብ ለብልሽት ይዳረግ እንደነበረ ተገልጿል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ በ2008 ዓ.ም የአምስት የዓሳ ማቆያና ማከፋፈያ ‹ሼዶች› ግንባታ ተጀምሯል፤ ነገር ግን በተያዘላቸው የአንድ ዓመት የጊዜ ገደብ አልተጠናቀቁም፤ ይህንንም በተደጋጋሚ መዘገባችን ይታወሳል፡፡

በብሔረሰብ አስተዳደሩ የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ መታፈሪያ አበባው የተከዜን የዓሳ ሀብት ለመጠቀም ከክልሉ መንግሥት ጋር በመሆን አምስት የዓሳ ማቆያ እና ማከፋፈያ ግንባታዎችን በዝቋላ፣ ስሃላ ሰየምት፣ አበርገሌ (ሁለት) እና ሰቆጣ ከተማ እየተገነቡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የዕቅድ ዝግጅት ክትትልና ግምገማ ዳይሬክተር አቶ መንግሥቱ ድልነሳ የዓሳ ማቆያና ማከፋፈያ ጣቢያዎቹ ግንባታ መዘግየት ምክንያቱ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እና የዓለም አቀፍ ግዢ ጨረታ በተደጋጋሚ አለመሳካት መሆኑን ተገልጿል፤ ችግሮቹ አሁን ተቀርፈው ወደ ሥራ መገባቱንም ገልጸዋል፡፡

አሁን ላይ ጣቢያዎቹ ግንባታቸው ተጠናቅቆ አስፈላጊ ግብዓቶች እየተሟሉ መሆናቸውንና ከአራት ወራት በኋላ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ እንደሚገቡም አስታውቀዋል፡፡

ለወጣቶቹ የሥራ ዕድል መፍጠሪያ የሚሆኑ አራት የዓሳ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎችም ግዥ ተፈፅሞ የሥራውን መጀመር በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ አመልክተዋል፡፡ የዓሳ ምርቱን እስከ ባሕር ዳር እና አዲስ አበባ ለማቅረብ እንደሚሠራም ነው አቶ መንግሥቱ የገለጹት፡፡

ለፕሮጀክቶቹ ግንባታ እስካሁን 36 ሚሊዮን ብር ወጭ መደረጉን ያገኘናቸው መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

ዘጋቢ፡- ግርማ ተጫነ

ፎቶ፡- የዝቋላ እና አበርገሌ ወረዳ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤቶች

Previous articleበአማራ ክልል ሰላማዊ ሰልፎቹ በሰላም ተጠናቅቀዋል፡፡
Next articleከ550 ኮንቴነር በላይ መድኃኒቶችና የሕክምና ግብዓቶች ወደ ኤጀንሲው መግባታቸው ተገለፀ፡፡