
የንግድ ማኅበረሰቡ የተያዘለትን የጊዜ ገደብ ተጠቅሞ የንግድ ፈቃዱን ማደስ እንደሚጠበቅበት የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ አሳሰበ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 09/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ የ2014 በጀት ዓመት የንግድ ፈቃድ እድሳትን በተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል። መግለጫዉን የሰጡት የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊ አቢታ ገበያው ናቸው።
ከሐምሌ 1/2013 ዓ.ም ጀምሮ በክልሉ የሚገኙ ነጋዴዎች የንግድ ፈቃዳቸውን እያደሱ እንደሚገኙ ገልጸዋል። ከሐምሌ 1/2013 ዓ.ም እስከ ታኅሣሥ 30/2014 ዓ.ም ባለው የጊዜ ገደብ ውስጥ 430 ሺህ ነጋዴዎች የንግድ ፈቃዳቸውን ያድሳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አቶ አቢታ በሰጡት መግለጫ አስረድተዋል። “ነጋዴው ጊዜ አለኝ እደርሳለሁ፣ ወረፋ ነው ብሎ ሳይዘናጋ የተሰጠውን ጊዜ ተጠቅሞ የንግድ ፈቃዱን በወቅቱ ማደስ ይኖርበታል” ብለዋል።
ነጋዴው ጊዜውንና ጉልበቱን በአግባቡ ለመጠቀም ግብሩን በሚከፍልበት ወቅት የንግድ ፈቃዱን ቢያሳድስ የተሻለ መሆኑንም ጠቁመዋል። ነጋዴው ፈቃዱን ካላሳደሰ መንግሥት ማግኘት ያለበትን ገቢ ስለሚቀንስ ዜጎች የሚጠይቁትን የመሠረተ ልማት ግንባታ ማከናወን እንደሚቸገር ተናግረዋል።
የንግድ ፈቃድን አለማደስ በሀገር ላይ የጎላ አሉታዊ ተፅዕኖ ያስከትላል ያሉት አቶ አቢታ ከሐምሌ 1/2013 ዓ.ም ጀምሮ በክልሉ በየደረጃው በሚገኙ የንግድና ገበያ ልማት መሥሪያ ቤቶች የንግድ ፈቃዱን የሚያሳድስ ነጋዴን በማስተናገድ ላይ ስለሚገኙ ነጋዴው የተሰጠውን ገደብ ሊጠቀምበት ይገባል ብለዋል።
የተቀመጠውን የጊዜ ገደብ ተጠቅመው የንግድ ፈቃዳቸውን የማያሳድሱ ነጋዴዎች በየደረጃው ለቅጣት እንደሚዳረጉ አስገንዝበዋል። ጭራሽ የማያሳድሱ ነጋዴዎች ደግሞ የንግድ ፈቃዳቸው እስከመጨረሻው እንደሚሰረዝ ነው የሕዝብ ግንኙነት ኀላፊው የገለጹት።
በ2012 ዓ.ም 400 ሺህ 254 ነጋዴዎች የንግድ ፈቃዳቸውን እንዲያሳድሱ ታቅዶ 351 ሺህ 185 ነጋዴዎች ማሳደሳቸውን ተናግረዋል።
ባለፈው ዓመት የንግድ ፈቃድ ማሳደሻ ጊዜው ያለፈባቸው 49 ሺህ 69 ነጋዴዎች የንግድ ፈቃዳቸው እንደተሰረዘባቸው አቶ አቢታ በመግለጫቸው አስረድተዋል።
የአማራ ክልል ንግድና ገበያ ልማት ቢሮ ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ነጋዴው ቤቱ ኾኖ በኦንላይን የንግድ ፈቃዱን እንዲያሳድስ የሚያስችል ሥራ እየተሠራ ነው ብለዋል። ይህም ኢንተርኔት ተጠቃሚ ለኾኑ አካባቢዎች መሆኑን ነው አቶ አቢታ የገለጹት።
ዘጋቢ:- ቡሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡ ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ