
አሸባሪው ትህነግ እየፈጸመ ያለውን ህጻናትን ወደ ጦርነት የመማገድ ተግባር ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ሊያወግዘው እንደሚገባ ተገለጸ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 09/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል ሀገራት “የህጻናት መብት ኮንቬንሽንን” ተቀብለው ያጸደቁት እንደ አውሮፓዊያኑ አቆጣጠር በ1989 ነበር፡፡ አባል ሀገራቱ ለህጻናት መብት መከበር መሠረት የሚጥሉ መመሪያዎችን አፅድቀዋል፡፡ የእኩልነት መብት፣ ለህጻናት ቅድሚያ መስጠት፣ የመኖር፣ የማደግ መብት እና የህጻናትን የሃሳብ ነጻነት ማክበር መሠረት ከሚጥሉት ድንጋጌዎች መካከል ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በዚሁ ድንጋጌ አንቀጽ 38 መሠረት ህጻናት በጦር ኃይሎች ውስጥ ያለመመልመል፣ ያለመሳተፍ እና ወደ ጦርነት ያለመግባት መብት እንዳላቸው ተደንግጓል፡፡ ነገር ግን አሸባሪው ትህነግ ከሰሞኑ በአማራ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች ለሚጎስመው የጦርነት ነጋሪት ህጻናትን በጦርነት ማሰማራቱን የሚገልጹ መረጃዎች እየወጡ ነው፡፡
አሸባሪው ትህነግ በሕግ ማስከበር እርምጃው የደረሰበትን ሽንፈት ሒሳብ ለማወራረድ እየተፍጨረጨረ እንደሆነም ዝቷል። ምንም እንኳን አሸባሪው የትህነግ ቡድን ህፃናትን ለጦርነት እየመለመለ እና እያሰለጠነ ሲማግድ ይህ የመጀመሪያው ባይሆንም ኒው ዮርክ ታይምስ ሰሞኑን ባወጣው ምስል አሸባሪው ከሰሞኑ ህጻናትን በጦርነት እንዲሰማሩ እያደረገ ነው፡፡
ይህም ህጻናትን ወደ ጦርነት በመማገድ ዓለም ዓቀፍ ወንጀል እየፈጸመ ስለመሆኑ ይፋ እየተደረገ ነው። በዘገባውም ህጻናት የጦር መሳሪያ ተሸክመው ሲንቀሳቀሱ የሚያሳይ ፎቶ አብሮ ተለቋል። ኢትዮጵያ የህጻናት ልዩ መብት ጥበቃ እንዲከበር የሚደነግጉ ዓለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊ እና ሀገራዊ ሥምምነቶችን ተቀብላ አጽድቃለች ያሉት በአማራ ክልል ሴቶች፣ ህጻናትና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ የህጻናት መብት እና ደኅንነት ማስጠበቅ ዳይሬክተር አቶ አሻግሬ ዘውዴ ናቸው፡፡ የህጻናት መብት ኮንቬንሽን፣ የአፍሪካ ህጻናት መብቶች ደኅንነት ቻርተር፣ የዓለም ሥራ ድርጅቶች ስምምነት፣ የአስከፊ ገጽታ ማስወገጃ ሥምምነት እና የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ለህጻናት ልዩ መብት ጥበቃ የሚያደርጉ እና ኢትዮጵያ የተስማማችባቸው ናቸው ብለዋል ዳይሬክተሩ፡፡
የህጻናት መብት መከበር ከሌላው የሕብረተሰብ ክፍል ተለይቶ አስፈላጊ የሆነበት ምክንያት ህጻናት በአካላዊ እና ሥነ ልቦናዊ እድገት ያልበሰሉ ከመሆናቸው በላይ የነገዋ ዓለማችን ተስፋ በህጻናቱ እድገት ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ነው ይላሉ አቶ አሻግሬ፡፡ ህጻናት ኢ-ሰብዓዊ ከሆነ አያያዝ ወጥተው በመልካም አስተዳደግ ላይ እንዲያልፉ የሚያስገድድ ሥምምነት መኖሩ ለህጻናቱ ጥቅም ብቻ ታስቦ ሳይሆን እንደማኅበረሰብ እና እንደትውልድ ሀገርን የሚረከቡ ተተኪዎችን ለማፍራት አስፈላጊ በመሆኑ ጭምር እንደሆነም አብራርተዋል፡፡
አሸባሪው ትህነግ ትናንት ብቻ ሳይሆን የሕልውና ዘመቻው ሲጀመርም ህጻናትን ወደ ጦርነት ሲማግዳቸው ታይቷል ብለዋል አቶ አሻግሬ፡፡ የሚያስገርመው ግን የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዝምታ እና ቸልታ ነው ይላሉ፡፡
ምንም አይነት ፖለቲካዊ ልዩነቶች ቢኖሩም እንኳን ህጻናትን ምንም ሊገባቸው በማይችል ግጭት ውስጥ ማስገባት ትልቅ የሞራል ዝቅጠት መኖሩን አመላካች ነው ብለዋል ዳይሬክተሩ፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ተቋማት ሊያወግዙት እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡
ህጻናቱ ልምድ እና እውቀት ካለው የጸጥታ ኃይል ጋር ተዋግተው የሚያደርሱት ጉዳት እንደማይኖር ቢታመንም ኢትዮጵያ ጉዳዩን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ በማሳወቅ ኀላፊነቷን ልትወጣ ይገባል ብለዋል፡፡ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም ከቆመለት ዓላማ የሚጻረር ድርጊት እያየ እና እየሰማ ዝምታን መምረጡ “መርጦ አልቃሽ” እንዳይሆን ጉዳዩን ማጤን ይኖርበታል ብለዋል አቶ አሻግሬ፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ