
“ሀገር ለማፍረስ የመጣን ኃይል በሕብረት ከመታገል ውጪ ምንም አማራጭ የለም›› የሱማሌ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ሙስጠፌ መሐመድ
ባሕር ዳር: ሐምሌ 09/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ሀገር ለማፍረስ የመጣን ኃይል በጋራ ከመታገል ውጪ ምንም አማራጭ እንደሌለ የሶማሌ ክልል ምክትል ርእሰ መሥተዳድር ሙስጠፌ መሐመድ ገለጹ፡፡
የሽብር ቡድኑን ጥቃት ለማምከን በሚደረገው እንቅስቃሴ የሱማሌ ክልል የበኩሉን ድርሻ ለመወጣት የጸጥታ ኃይል ወደ ቦታው ለማሰመራት ዝግጅት እያደረገ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ እንደገለጹት፤ አሸባሪው ትህነግ በሀገር መከላከያ የሰሜን ዕዝ ሠራዊት ላይ ያደረሰውን ጥቃት ተከትሎ የተጀመረው የሕግ የማስከበር ዘመቻ የተለያዩ ምዕራፎችን አልፏል፡፡ በዚህ ሂደት የአሸባሪው የትህነግ ቡድን ከመጀመሪያው ጀምሮ የሚሰጣቸው ምክንያቶች ይለዋወጡ፣ ሐሳቦቹ ይቀያየሩ እንጂ የሚከተለው ሀገር የማፍረስ አጀንዳ በመሆኑ ሀገር ለማፍረስ የመጣን ኃይል በሕብረት ከመታገል ውጪ ምንም አማራጭ የለም ነው ያሉት፡፡
የሽብር ቡድኑ የሚከተለው አጀንዳ እሱ ከሚያነሳቸው ሰብዓዊ መብትና ራስን በራስ ከማስተዳደር አጀንዳዎች ጋር በፍጹም የሚገናኝ አይደለም ያሉት አቶ ሙስጠፌ ፤ እነዚህን አጀንዳዎች የሚያነሳቸው ዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ለማወናበድ እንጂ የእሱ ዓላማ ሀገርን ማፍረስ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
የሽብር ቡድኑ የተናጠል የተኩስ አቁሙ ውሳኔ ለትግራይ ሕዝብ ሰብዓዊ ድጋፍና ለአርሶ አደሮች እርሻ ሥራ ሲባል በመንግሥት የተደረገ ውሳኔ መሆኑን እያወቀ ውሳኔውን እንደ ፍርሐት በመቁጠር ተደፋፍሮ ክልሎችን ለማጥቃትና ሀገሪቱን ለማፍረስ እየሞከረ ነው ብለዋል፡፡
የሽብር ቡድኑ ለትግራይ ሕዝብ ክብርና ሐዘኔታ ቢኖረው ኖሮ በሌሎች ክልሎች ላይ ዳግመኛ ትንኮሳ ማሄድ የለበትም ነበር ያሉት ምክትል ርእሰ መሥተዳድሩ በአፋርና በአማራ ክልሎች ትንኮሳ ማካሄዱ አጀንዳው ኢትዮጵያን ለማፈራረስ እንደሆነ በግልጽ የሚያሳይ ነው። በመሆኑም ሀገር ለማፍረስ የሚንቀሳቀሰውን ይህንን ኃይል በሕብረት መታገል እንደሚያስፈልግ ማስገንዘባቸውን ኢፕድ ዘግቧል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ