
በዋግ ኽምራ ግንባር የተሰለፉ የአማራ ሚሊሻ አባላት አሸባሪውን ትህነግ ለመደምሰስ መዘጋጀታቸውን ገለጹ።
ባሕር ዳር: ሐምሌ 09/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ከዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ደሃና ወረዳ የመጡት የሚሊሻ አባል አቶ ፀጋዬ ወዳጅ የትህነግ አሸባሪ ቡድን የአማራ ሕዝብን ጀግንነት ዘንግቶ ድንበር ተሻግሮ ትንኮሳ በመፈጸሙ አይቀጡ ቅጣት ልንቀጣው ነፍጣችንን አንግበን መጥተናል ብለዋል።
የአማራ ሕዝብ ከአሸባሪው ትህነግ ጋር በጀግንነት ተዋግተን ህልውናችንን እንድናስከብር በክብር ሲሸኙን ትህነጎች ግን ሕጻናትን እና አረጋውያንን በጦር ሜዳ ከኛ ጋር በማሰለፍ በሕግ ብቻ ሳይሆን በፈጣሪ ዘንድም የማይወደድ ሥራ በመሥራት ላይ ይገኛሉ ነው ያሉት።
የአማራ ሚሊሻ ህልውናውን ለማስከበር በሚያደርገው ተጋድሎ ደጀን የሚሆነው በርካታ ሕዝብ ከጎኑ ያሰለፈ ነው። በርካታ ጀግኖችን ከኋላችን አድርገን ነው ህልውናችንን የምናስጠብቀው ብለዋል።
ከአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ ከምሥራቅ ጎጃም ዞን ከመጡ ሚሊሻዎች እና ከጀግናው የአማራ ልዩ ኃይል ጋር በጋራ ሆነን ትህነግን ለመደምሰስ ዝግጅታችንን አጠናቀናልም ነው ያሉት።
ወጣት ነብዩ የኔው ከአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር በዋግ ግንባር የተሰለፈ የአማራ ሚሊሻ አባል ነው። የሁሉም ኢትዮጵያውያን ጠላት የሆነው ትህነግ በዋግ አከባቢ ትንኮሳ መጀመሩን ሲሰማ ከታጋይ ጓዶቹ ጋር በመሆን ዋግ ግንባር ደርሷል። ትህነግን በማያዳግም እርምጃ ለመደምሰስ ዝግጁነቱን ገልጿል።
“የትህነግ አቅም ወሬዋ ብቻ ነው” የሚለው ወጣት ነብዩ እኛ ግን የአማራን ህልውና ብቻ ሳይሆን የሀገር ህልውናን ማስከበር በሚያስችለን መልኩ ተዘጋጅተን ነው ወደ ግንባር የመጣነው ብሎናል።
የትህነግ መጨረሻው በሚጠላው የአማራ ምድር ላይ እንደሚሆንም ነው የተናገረው።
ሌላው የሚሊሻ አባል አቶ አበባው ወረታ እኛ የአማራ ሚሊሻዎች ተደራጅተን አሸባሪውን ቡድን ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማንነታችንን ልናሳየው ተዘጋጅተናል ብለዋል።
ዘጋቢ:- እሱባለው ይርጋ – ከዋግኽምራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ