
የቀድሞ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ዛሬም እንደ ትናንቱ አሸባሪውን ቡድን ለመፋለም ተዘጋጅተዋል።
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 09/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የቀድሞ የመከላከያ ሠራዊት አባላት በሀገር ላይ የሚቃጣን ማንኛውንም ጥቃት ለመመከት መዘጋጀታቸውን አስታውቀዋል።
ባለፉት 27 ዓመታት በትህነግ ከፋፍለህ ግዛ ኢትዮጵያዊነት አደጋ ላይ ወድቆ ቆይቷል። አሸባሪው ትህነግ በሰራው ሴራ በሕዝቦች መካከልም መተማመን እንዳይኖር አድርጎ ቆይቷል።
በመከላከያ ተቋምም ትህነግ ከፍተኛ ሴራ መሥራቱን በመከላከያ ሠራዊቱ ውስጥ ሲያገለግሉ የነበሩ የቀድሞ አባላት ነግረውናል።

አሚኮ ካነጋገራቸው የቀድሞ መከላከያ ሠራዊት አባላት መካከል ሌተናል ኮሎኔል ከበደ ይመር እንዳሉት ከ1981 ዓ.ም ጀምሮ በኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ውስጥ በመቀላቀል ለ20 ዓመታት አገልግለዋል። እነዚህ ጊዜያት ግን ሀገራዊ እንድነት የተጠናከረበት ሳይሆን ይልቁንም የትህነግ ሀገር አፍራሽነት ሴራን የተረዱበት ጊዜ እንደነበር ነግረውናል።
ሌተናል ኮሎኔል ከበደ ትህነግ ጫካ ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ አራት ኪሎ እስከተባረረበት ድረስ ነገረ ስራው ሁሉ ሀገርን በማፍረስ ሥራ ላይ የተጠመደ ነበር፤ አሁንም እሱን ነው የቀጠለው ብለዋል።
በኢትዮጵያ ሕዝብ በሰው ልጆች ላይ ሊፈጸም የማይችል አረመኔያዊ ድርጊት ይፈጽም እንደነበርም ገልጸዋል።
አሸባሪው ትህነግ ለዘመናት በቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ ሆኖ ከ20 ዓመታት በላይ ሕዝብንና ሀገርን ሲጠብቅ በነበረው የሀገር አለኝታ መከላከያ ሠራዊት ላይ የፈጸመው ጥቃት የለየለት አሸባሪነቱን እና ሀገር አፍራሽነቱን በግልጽ ያሳየ መሆኑን አንስተዋል።

ይህ የትህነግ ባህሪ ዛሬ የተጀመረ ሳይሆን ጫካ እያለ ጀምሮ የትግል ጓዶቹን በተኙበት እየረሸነ የመጣ ሰው በላ ቡድን እንደሆነም ጠቅሰዋል።
የቀድሞ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ዛሬም እንደ ትናንቱ የሀገርን ሉዓላዊነት የማስጠበቅ ታሪካዊ ኀላፊነታቸውን ለመወጣት ከየአካባቢው የጸጥታ መዋቅር ጋር እየሠሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
ሻለቃ አበጀ ከ1982 ዓ.ም ጀምሮ ለ22 ዓመታት በሀገር መከላከያ ሠራዊት ውስጥ እንዳገለገሉ ነግረውናል። ሻለቃው እንዳሉት ትህነግ በሕዝቦች መካከል ሴራ ሲሰራ የቆየ ከፋፋይ ድርጅት ነው። ያለምንም ምክንያት ከሠራዊቱ በማሰናበት የሠራዊቱን የዕዝ ሰንሰለት በአንድ ብሔር ተወላጆች ብቻ በመቆጣጠር የሠራዊቱን ህብረ ብሄራዊነት እና ኢትዮጵያዊነት ያደበዘዘ እንደነበር ነው የተናገሩት።
ታጋይ ገነት ደሞዝ የሀገር መከላከያ ሠራዊት በወሰደበት ርምጃ በደረሰበት ሽንፈት ያበሳጨው ትህነግ “በአማራ ላይ ሂሳብ አወራርዳለሁ” ማለቱ የቆየ የጥላቻ መንፈስ እንደሆነ አንስተዋል። ይህንም በህብረት ለመመከት አየሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
ሀምሳ አለቃ ደምለው ኃይሉ ደግሞ የትህነግ የአማራ ጥላቻ ከበታችነት ስሜት የመነጨ እንጅ ሕዝብ እንደ ሕዝብ በደል ፈጽሞ አለመሆኑን አንስተዋል። ዛሬም እንደትናንቱ በሀገር ሉዓላዊነት ላይ የሚደቀን ማንኛውንም አደጋ ለመከላከል መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ