
“አሸባሪው ህወሓት በሚፈጥረው ግጭት ምክንያት ችግር ውስጥ የሚገባው ከአማራ ክልል ጋር ብቻ ሳይሆን ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር እንደሆነ የኦሮሚያ ወጣት ማኅበር ፕሬዚዳንት ወጣት ከድር እንዳልካቸው አስታወቀ።
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 08/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የኦሮሚያ ወጣቶች ማህበር ፕሬዚዳንት ወጣት ከድር እንዳልካቸው ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንደገለጸው፤ የአሸባሪው ህወሃት የግጭት ተልእኮ ከአማራ ክልል ጋር ብቻ እንደሚያያዝ በተደጋጋሚ ሲናገር ይደመጣል። ይሁንና ቡድኑ የሚፈጥረው ችግር አማራ ክልልን ብቻ ሳይሆን መላው የኢትዮጵያ ህዝብን የሚነካ እና የሚመለከት ጉዳይ ነው። በመሆኑም ችግሩ የጋራ በመሆኑ በጋራ እንመክተዋለን ብሏል።
በኢትዮጵያ ጥላ ስር ያለው ወጣት በሙሉ የአሸባሪውን ህወሃት የጥፋት አጀንዳ እየተቃወመው ይገኛል ያለው ወጣቱ፤ መቃወምም ብቻ ሳይሆን አሸባሪውን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እኩይ ተግባሩን እንዲያቆም ክልሎች ልዩ ኃይላቸውን በመላክ ላይ ናቸው። ይህ የሚያሳየው ቡድኑ የሚፈጥረው ችግር ከአማራ ክልል ጋር ብቻ ሳይህን እያንዳንዱን ኢትዮጵያዊ የሚነካ መሆኑን ነው ብሏል።
ኢትዮጵያ በቀላሉ የማትፈርስ ሀገር ናት ፤ እንደ ኦሮሞ ወጣት እኛ በዚች ሀገር ላይ እያለን ኢትዮጵያ አትፈርስም ። ሀገሩ እንድትፈርስ የማይፈልግ ዜጋ ሁሉ አሸባሪውን ህወሃት መታገል አለበት። ለእራሳችንም ህልውና እና ለሀገራችን ሉአላዊነት ስንል ከመከላከያ ሰራዊት ጎን እንሰለፋለን ብሏል።
ለጥፋት የማይመለሰው አሸባሪው ህወሃት በጦር ግንባሮች አካላቸው ያልጠነከሩ ህጻናትና ወጣቶችን ማሰለፉ የኦሮሚያ ወጣቶች ማህበሩ እንሚያወግዘው ወጣት ከድር ገልጿል።
ህጻናትን ከፊት በማሰለፍ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት መጣጣርም በዓለም አቀፍ ህግ ጭምር የሚያስጠይቅ በመሆኑ ተቀባይነት እንደሌለው አስታውቋል።
ለትግራይ ሕዝብ የተሰጠውን የጥሞና ጊዜ ህዝቡ እንዳይጠቀምበት አሸባሪው ህወሃት በማጨናገፍ ህጻናትን ሳይቀር ለግጭት ማሰለፉን በማህበራዊ ድረገጾች በስፋት እየተስተዋለ ነው። ለዓለም የህጻናት መብት የቆሙ ተቋማት ይህን ኢሰብአዊ ተግባር መቃወም አለባቸው ብሏል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ