
“በዞኑ ከሕዝብ ጋር እየኖረ ለአሸባሪው ቡድን የሚያገለግል አካል ካለ የማያዳግም ርምጃ ይወሰድበታል” የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን ዋና አስተዳዳሪ
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 08/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን ሑመራ ከተማ ዝክረ ሐምሌ 5 ተከብሯል።
በድል ቀኑ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት፣ ለአማራ ልዩ ኀይል፣ ለአማራ ሚሊሻ እንዲሁም ለፌዴራል ፖሊስ በሕግ ማስከበር ዘመቻው ላስገኙት አንጸባራቂ ድል ምስጋና ቀርቦላቸዋል።
በዝግጅቱ ላይ የተገኙት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አሽተ ደምለው ኢትዮጵያ ብዙ ፈተናዎችን አሳልፋለች ብለዋል፡፡ በተለይም ፈተናው ለወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ሕዝብ አዲስ አይደለም፤ ባለፉት ዓመታት ብዙ መከራና ውጣውረድ አሳልፏል ብለዋል፡፡

ሀገርን አፈርሳለሁ ብሎ የተነሳው አሸባሪ የትህነግ ቡድን ከቤተ መንግሥት ወደ መቀሌ ብሎም ወደ ቆላ ተንቤን ወርዶ ፈራርሷል ብለዋል፡፡ በመኾኑም ኢትዮጵያን የማፍረስ አቅም የለውም ሲሉም ተናግረዋል፡፡
ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ትህነግ በሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ክህደት መፈጸሙን ተከትሎ የሠራዊቱ አባላት የሕግ ማስከበር ዘመቻ አካሂደው የትግራይ ሕዝብን ነጻ አውጥተዋል፤ ይሁን እንጅ ሰላም ማስከበር ላይ እያለ በሕዝቡ ዳግመኛ ክህደት እንደተፈጸመበት አቶ አሸተ አስረድተዋል፡፡ ሀገር ወዳዱ የአማራ ሕዝብ ግን የመከላከያ ሠራዊቱን እግሩን አጥቦ እጁን ስሞ ባለው አቅም ይደግፈዋል እንጅ ከጀርባው አይወጋውም ነው ያሉት፡፡
የሰሜን እዝ የሀገር መከላከያ ሠራዊት በትግራይ ክልል በቆየባቸው 21 ዓመታት ከደመወዙ ቀንሶ ትምህርት ቤት፣ ጤና ጣቢያ ገንብቷል፤ የማኀበረሰቡ ሰብል በአንበጣ በተወረረበት ጊዜ ደግሞ ሰብሉን ተከላክሏል፤ በሌሎች ማኀበራዊ ጉዳዮችም እገዛ ሲያደርግ እንደቆየ አቶ አሸተ አብራርተዋል፡፡ ሕዝቡም ለመከላከያ ሠራዊቱ ደጀን አለመሆኑ ስህተት እንደኾነ አስረድተዋል፡፡
አማራ በኢትዮጵዊነቱ የማይደራደር በመልካም ማንነት ላይ የተመሠረተ የሥነልቦና ውቅር ያለው ሕዝብ ነው ብለዋል፡፡
አሸባሪው የትህነግ ቡድን ሕጻናትን ሳይቀር በአደንዛዥ እጽ እያሳበደ ለጦርነት እየማገደ እንደኾነም አብራርተዋል፡፡

የተከዜን ወንዝ ተሻግሮ የሚመጣ ማንኛውም የትህነግ ርዝራዥ መቀበሪያው ወልቃይት ጠገዴ ይኾናል ያሉት አቶ አሸተ ሕዝቡም ቀደም ብሎ በተደራጀም ኾነ ባልተደራጀ መልኩ ሲታገል መቆየቱን አንስተዋል፡፡ አሁንም ከፌዴራል የጸጥታ አካላት ጋር በመኾን የመደምሰስ እርምጃው ተጠናክሮ ቀጥላል ብለዋል፡፡
ዓለማቀፍ ተቋማት እና የአውሮፓ ሀገራት ሀቁን መረዳት ተስኗቸው ተገቢ ያልኾነ ሀሳብ ቢያራምዱም የኢትዮጵያ መንግሥት ግን የሀገሪቱን ህልውና ለመጠበቅ እየሠራ ነው ብለዋል፡፡ ከሰሞኑ የአማራ ክልል መንግሥት ከመከላከል ወደ ማጥቃት መሸጋገሩንም አስገንዝበዋል፡፡
አቶ አሸተ በዞኑ ከሕዝብ ጋር እየኖረ የአሸባሪው ቡድን አይን እና ጀሮ ኾኖ የሚያገለግል ኀይል ካለ የማያዳግም ርምጃ እንደሚወሰድበት ግንዛቤ ሊወሰድ እንደሚገባም ገልጸዋል፡፡
ክልሉ ከፌዴራል የጸጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የማጽዳት እርምጃውን አጠናክሮ ይቀጥላል ያሉት አቶ አሸተ ለጊዜውም ቢኾን ነፍስ ዘርቶ መንግሥት ይመሠርታል የሚል አካል ካለ ተስፋ ይቁረጥ ብለዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ -ሑመራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ