
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የትህነግ አሸባሪ ቡድንን ለመመከት መላው ሕዝብ ያልተቆጠበ ሁለንተናዊ ድጋፍ እንዲያደርግ
ጥሪ አቀረበ።
ባሕር ዳር: ሐምሌ 08/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በሰጠው የአቋም
መግለጫ እንዳለው ፤ አሸባሪ ቡድኑ የሚያደርሰውን ጥቃት በመመከት የተጀመረው ሀገር የማዳን ተልእኮ ግቡን እንዲመታ
መላው ሕዝብ ኀላፊነቱን ሊወጣ ይገባል።
“ሕዝቡ ለሀገሩና ለሠራዊቱ ሁሌም እንደሚያደርገው ያልተቆጠበ ሁለንተናዊ ድጋፍ በገንዘብ፣ በጉልበትም ኾነ በዕውቀት አቅም
በፈቀደው ኹሉ በማድረግ ሀገራዊ ኀላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል” ብሏል፡፡
“ወጣቶችና አቅማችን የሚፈቅድ ሠራዊታችንን በመቀላቀል ሌሎቻችን ደግሞ የሞራልና የስንቅ ድጋፋችንን አጠናክረን በመቀጠል
ደጀንነታችንን በተግባር የምናሳይበት መሆን ይኖርበታል” ሲል ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
ኢትዮጵያውን፤ በዚህ ወቅት ከመቼውም ጊዜ በላይ በአሸባሪው ቡድን በሚነዙ የሐሰት ፕሮፖጋንዳ መወናበድ እንደሌለባቸውም
አስገንዝቧል።
“ውስጣዊ አንድነታችንን በማጠናከር፤ እርስ በርስ በመመካከርና በመደጋገፍ የተቃጣብንን ሀገራዊ ጥቃት በሕብረትና በአንድነት
እንደ አንድ ልብ ሆነን ልንመክት ይገባል” ሲል መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡
ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ የተሰጠው የአቋም መግለጫ ሙሉ ቃል፡-
ኢትዮጵያን የማፍረስ ቅዠት በኢትዮጵያውያን የጋራ ትብብር ይመክናል!
በሰሜን ኢትዮጵያ ከተካሄደዉ የሕግ ማስከበር ዘመቻ በኋላ መንግሥት ሕዝቡ በጦር እንቅስቃሴ ሳይረበሽ በጥሞና ጊዜ ፋታ
አግኝቶ እርሻውን የሚያከናውንበት የእርዳታና ድጋፍ አቅርቦቱም ያለሰበብ ሳይደናቀፍ የሚከናወንበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ሲባል
በሰብዓዊነት ላይ የተመሠረተ የተናጠል የተኩስ አቁም እርምጃ ወስዷል፡፡
ኾኖም ግን ይህ አሸባሪ ቡድን በኢትዮጵያ መንግሥት የታወጀውን ሕዝብን ያስቀደመ የተናጠል የተኩስ አቁም ስምምነት
ተጠቅሞ ከስህተቱ ተምሮ የትግራይን ሕዝብ ከከፋ ስቃይ እና መከራ መታደግ ሲገባው፤ የመንግሥትን አርቆ አስተዋይነት
እንደሽንፈት ቆጥሮ ከተደበቀበት ጎሬ ወጥቶ እንደ ድል አድራጊ በየአካበቢው መፎከር ብቻ ሳይሆን ከዚያም አልፎ በተለያዩ
ቦታዎች ላይ ጥቃት በመፈፀም የተዘረጉትን መልካም የሰላም እድሎችን ኹሉ ዝግ በማድረግ እንደገና ጥቃት ከፍቷል፡፡
ጥቃቱ የተከፈተብን መላ ኢትዮጵያውያን ዓለምን ባስደነቀ መልኩ እጅግ ሰላማዊ የሆነ ምርጫ አከናውነን የጋራ አሸናፊነታችንን
ባረጋገጥንበት ለዲሞክራሲ ግንባታ ያላንን ቁርጠኝነት በተግባር ባሳየንበት ወቅት መሆኑም ብቻ ሳይሆን ሁለተኛ ዙር የህዳሴ
ግድብን በመሙላት ላይ ባለንበትና መላው ኢትዮጵያውያን የሀገራችንን የትንሣኤ ዘመን ብስራት የሆነው የህዳሴ ግድባችን ላይ
እየተቃጣ ያለውን ጣልቃ ገብነት በመቃወም ለሉዓላዊነታችን መከበር በአንድነት ትከሻ ለትከሻ በቆምንበት ወቅት መሆኑ ጉዳዩን
በተለየ ስሜት እንድንመለከተውና ኀላፊነታችን ላቅ ያለ መሆኑን ያስገነዝበናል፡፡
ይህ የሽብር ቡድን ለዚህ እኩይ ዓላማው፤ እንክብካቤ የሚያሻቸው ፤ የጦር መሳርያ ሳይሆን ደብተር ማንገብ የሚገባቸውን
ሕጻናት፣ የሃይማኖት አባቶችን፣ አዛውንቶችን ደካሞችን ጨምሮ በግዳጅ በጦርነት በመማገድ ለሀገራችን ብቻ ሳይሆን ለዓለም
አቀፍ ሕግጋት ተፈጻሚነት ደንታ የሌለው ጨካኝ ቡድን መሆኑን በይፋ እያስመሰከረ ይገኛል፡፡
አንዳንድ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ሚዲያዎቻቸዉ ጭምር ይህ የሽብር ቡድን መንግሥት ተግባራዊ ያደረገዉን የተናጠል የተኩስ
አቁም እርምጃ ወደ ጎን በማለት በንጹሐን ላይ እምነትን ጭምር መሰረት አድርጎ ግድያና ጭፍጨፋ ሲያካሂድ፤ ባለዉ አቅም ኹሉ
ትንኮሳ ከማድረግ አልፎ ጥቃት ለመፈጸም ሲዘጋጅና ሲጀምር የተቋቋሙበትን ዋና ዓላማ እና የጋዜጠኝነትን ሥነ-ምግባር በጣሰ
መልኩ ጉዳዩን አይቶ እንዳላየ ሲያልፉት ተመልክተናል፡፡ ይባስ ብለዉ አሁን ላይ መንግሥት የህልውና ዘመቻዉን በጀመረበት ሰዓት
የተኩስ አቁም ይደረግ በሚል የተለመደ የሽብር ቡድኑን የማዳኛ ታክቲካቸዉን ለመተግበር ሲሯሯጡ ታዝበናል፤ ይህ ኢ-ፍትሐዊ
ተግባር ለመላዉ የኢትዮጰያ ሕዝብ ድብቅ ዓላማቸዉን ይፋ ያደረገ ሆኗል፡፡
ወትሮም ቢሆን እኛ ያልመራናት ኢትዮጵያ ሰላም ሆና ማደር የለባትም ‘’እኔ ከሞትኩ፤ ሰርዶ አይብቀል’’ እንዲሉ በተደጋጋሚ እኔ
ካልመራሁ ኢትዮጵያ መፍረስ አለባት! በማለት ሲናገር የከረመውና ላለፉት ዓመታት አቅሙ በቻለው ኹሉ ከውስጥም ከውጪም
ካሉ ኢትዮጵያን ለማዳከምና ለማፍረስ ከሚንቀሳቀሱ ኀይሎች ኹሉ ጋር ሲሠራና ሲያሰማራ ተደጋጋሚ የጥፋት ሙከራዎችን
ሲያደርግ የቆየው ይህ ቡድን ከጥፋት ተልእኮው መቼም የማይመለስ መሆኑ ለማንም ግልፅ ነው፡፡
አሁንም ቢሆን የተጀመረው ማጥቃት እና ትንኮሳ፤ የአንድ ወገን የአንድ አካባቢ ጥቃት ብቻ አይደለም፡፡ ይህ ጥቃት በመላው
ኢትዮጵያውያን ላይ የተቃጣ ፤ ጸረ ኢትዮጵያ አቋም የገፋው በህልውናችን ላይ የተጋረጠ አደጋ ነው፡፡
ይህ አሸባሪ ቡድን የሀገራችን ሕዝቦች መተባበርና አንድነት እንቅልፍ የሚነሳው፤ ኢትዮጵያ ተበታትና እስካላየ አልያም ራሱ
እስካልመራ ድረስ መቼም ቢሆን አርፎ የማይቀመጥ፤ ይህንንም በተደጋጋሚ በተግባር ያረጋገጠ የኢትዮጵያውያን ኹሉ የጋራ
ጠላት ነው፡፡
እኛ ኢትዮጵያውያን እንደሁልጊዜውም በኢትዮጵያ የቁርጥ ቀን ልጅ በሆነው ሠራዊታችን ኩራት ይሰማናል፡፡ ለሠራዊታችንም
ማንኛውንም ድጋፍ ማድረግን አጠናክረን እንቀጥላለን፡፡
በዚህ ሰዓት አሸባሪ ቡድኑ የሚያደርሰውን ጥቃት በመመከት የተጀመረው ሀገር የማዳን ተልእኮ ግቡን እንዲመታ መላው
ሕዝባችን ለሀገሩና ለሠራዊቱ ሁሌም እንደሚያደርገው ያልተቆጠበ ሁለንተናዊ ድጋፍ በገንዘብ፤ በጉልበትም ኾነ በዕውቀት አቅም
በፈቀደው ኹሉ በማድረግ ሀገራዊ ኀላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል፡፡
ወጣቶችና አቅማችን የሚፈቅድ ሠራዊታችንን በመቀላቀል ፤ ሌሎቻችን ደግሞ የሞራልና የስንቅ ድጋፋችንን አጠናክረን
በመቀጠል ደጀንነታችንን በተግባር የምናሳይበት መሆን ይኖርበታል፡፡
መላው ኢትዮጵያውን፤ በዚህ ወቅት ከመቼውም ጊዜ በላይ በአሸባሪው ቡድን በሚነዙ የሐሰት ፕሮፖጋንዳ ሳንወናበድ፤ ውስጣዊ
አንድነታችንን በማጠናከር፤ እርስ በርስ በመመካከርና በመደጋገፍ፤ የተቃጣብንን ሀገራዊ ጥቃት በሕብረትና በአንድነት፤ እንደ
አንድ ልብ ኾነን ልንመክት ይገባል፡፡
በአንዳንድ ማኅበራዊ ሚዲያ የጸጥታ ኀይሉን በጋራ በትብብር በእውቀት ላይ የተመሰረተ ስምሪትና ተግባር የምትተቹና
እየከፋፈላቹህ በማኀበራዊ ሚዲያ የምትጽፉ ከዚህ ድርጊታቹህ በመቆጠብ ይልቁንም የጸጥታ ኀይሉን ስምሪት ለጸጥታ አካሉ
ትተን፤ በሀገራችን ላይ ከውስጥም ከውጭም በየአቅጣጫው የተከፈተውን የዲጂታል ሚዲያ ጦርነት በትብብርና በአንድነት
ልንመክት ይገባል፡፡
የከተማችን አዲስ አበባ ነዋሪዎች ለሠራዊታችን ከምናደርገው ያልተቆጠበ ድጋፍም ባሻገር የአካባቢያችንን ሰላምና ደኅንነት
በመጠበቅ ፤ ከጸጥታ ኀይሉ ጋር በትብብርና በቅርበት በመሥራት፤ ለህዳሴ ግድባችን ድጋፋችንን በማጠናከር ፤ የጀመርነውን
የከተማችንን ሁለንተናዊ ብልጽግና የማረጋገጥ እንቅስቃሴ እንቀጥላለን፤ ሀገራዊ ኀላፊነታችንን በንቃት እንወጣ ዘንድ ጥሪያችንን
እናስተላልፋለን!!
ጀግኖች አባቶቻችን ተባብረውና ተጋግዘው በጀግንነት ያቆዩልንን ነጻ ሀገር እኛ ልጆቻቸው የአባቶቻችንን ታሪክ በመድገም
የኢትዮጵያን ክብር ከፍ እናደርጋለን!
ኢትዮጵያ በጀግኖች ልጆቿ ሕብረት ታፍራና ተከብራ ትኖራለች!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!!
ሐምሌ 2013
አዲስ አበባ