
በእርዳታ ስም ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ የሚገቡ አካላትን መንግሥት እንደማይታገስ የውጭ ጉዳይ
ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 08/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው ትህነግ በዓለም የጦር ወንጀል የሚያስጠይቀውን ህፃናትን ለውትድርና
የማስገደድ ተግባር ዓለም አቀፍ ተቋማት በአወንታ ማየታቸው ፍፁም ተቀባይነት እንደሌለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
አስታውቋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ድኤታ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በሰጡት መግለጫ በቅርቡ መንግሥት
በትግራይ ክልል ባወጀው የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔ ለሰብዓዊነት ቅድሚያ ለመስጠት ሠራዊቱን ከክልሉ ማስወጣቱን
ገልጸዋል፡፡
“የሰብዓዊ እርዳታ ያለገደብ እንድናቀርብ ቁጥጥር አይደረግብን” የሚሉ የረድኤት ድርጅቶችን ጥያቄ ለማስተናገድና አርሶ አደሮች
በሰላም እርሻቸውን እንዲያርሱ የመከላከያ ሠራዊት ክልሉን ለቆ መውጣቱ ለበጎ ዓላማ ቢሆንም ውጤቱ ግን የተገላቢጦሽ ሆኗል
ብለዋል፡፡
የመንግሥትን የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔ በአሉታ በመመልከት አሸባሪው የትህነግ ቡድን በዓለም አቀፍ ሕግ ውግዝ የሆነውን
ህፃናትን ለውትድርና የማሰለፍ ተግባሩን አሁንም አጠናክሮ መቀጠሉን አምባሳደር ሬድዋን ገልጸዋል፡፡
ይህም ተግባር በዓለም አቀፍ ተቋማት ጭምር በአዎንታ መታየቱ ተገቢነት እንደሌለው አብራርተዋል፡፡
ትህነግ የተናጠል የተኩስ አቁሙን አፍርሶ በርካታ አፍራሽ ተግባራትን ፈፅሟል ያሉት ሚኒስትር ድኤታው፣ የረድኤት ድርጅቶችም
ቢሆን መንግሥት በስፈራው በነበረበት ወቅት ሲያቀርቧቸው የነበሩ አሉባልታ ክሶች አሁንም ደግመው መቀጠላቸውን አንስተዋል፡፡
የውጭ ሀገራትም ሆኑ በእርዳታ ስም ወደ ኢትዮጵያ ገብተው በውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ የሚገቡ አካላትን መንግሥት
እንደማይታገስም አስታውቀዋል፡፡
በተለይም በስብዓዊ እርዳታ ስም የሽብር ቡድኑን በመሳሪያ ለማስታጠቅ የሚደረጉ ሙከራዎች መኖራቸውንና መንግሥት
በሰጠው የጥሞና ጊዜ ለውጥ ከሌለ መንግሥት ሀገር የማዳን ውሳኔውን ዳግም እንደሚቃኘው አምባሳደር ሬድዋን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት ከውጭ እና ከውስጥ በተቀናጀ መልኩ በሚፈጸምበት አሻጥር ሀገር ስትፈርስ ዝም ብሎ እንደማይመለከት
ሚኒስትር ዲኤታው ተናግረዋል፡፡
ሕዝቡም በአሁኑ ወቅት በህዳሴው ግድቡ እና በምርጫው ያሳየውን የነቃ ተሳትፎ አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጠይቀዋል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m