“በህልውና ዘመቻው በግንባር ጠላታችንን ከመፋለም ባለፈ ድህነትን ለማሸነፍም ችግኝ መትከል ይገባል” የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ ሳኅሉ (ዶ.ር)

107
“በህልውና ዘመቻው በግንባር ጠላታችንን ከመፋለም ባለፈ ድህነትን ለማሸነፍም ችግኝ መትከል ይገባል” የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ ሳኅሉ (ዶ.ር)
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 08/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ከባሕር ዳር ሁሉም ክፍለ ከተሞች የተወጣጡ ነዋሪዎች፣ የመንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት የሥራ ኀላፊዎች እና ሠራተኞች ዛሬ በባሕር ዳር ከተማ ቤዛዊት ተራራ ችግኝ ተክለዋል፡፡
በችግኝ ተከላው ከተሳተፉ ወጣቶች መካከል አንዱ ዳንኤል ታዬ ነው፡፡ አሸባሪው ትህነግን ለመመከት እየተካሄደ ላለው የህልውና ዘመቻ ዝግጅት ጎን ለጎን አካባቢን አረንጓዴ ለማልበስ ችግኝ ተክሏል፡፡
በአማራ ክልል ሕዝብ የመጣውን የህልውና አደጋ ከሌሎች ወንድም ሕዝብ ጋር በመሆን ለመፋለም መዘጋጀቱንም ተናግሯል፡፡
ሌላዋ አስተያየት ሰጪ ወይዘሮ እናና ሙሉሰው እናቶች የሕልውና ዘመቻውን ለማገዝ በየአካባቢያቸው ስንቅ እያዘጋጁ ናቸው ብለዋል፡፡ ከስንቅ ዝግጅት በተጨማሪም “ኢትዮጵያን አረንጓዴ እናልብስ” በሚል መሪ ሐሳብ የተጀመረውን የአረንጓዴ ዐሻራ መርኃግብር እንዲሳካ በችግኝ ተከላ እየተሳተፉ መሆናቸውን ነግረውናል፡፡
የባሕርዳር ከተማ አስተዳደር ግብርና እና ገጠር መሬት አስተዳደር መምሪያ ኀላፊ ትልቅሰው ዕምባቆም እንደተናገሩት በባሕርዳር ከተማ አስተዳደር የተተከሉ ችግኞች 80 በመቶ በላይ መጽደቃቸውን ነው የገለጹት፡፡ በቀጣይም የጽድቀት መጠኑን ከዚህ በላይ ለማድረስ ትኩረት ያስፈልገዋል ብለዋል፡፡ በዚህ ዓመት የአረንጓዴ ዐሻራ መርኃግብር በከተማ አስተዳደሩ 132 ነጥብ 2 ሄክታር መሬት ላይ 3 ነጥብ 2 ሚሊዮን የደንና የፍራፍሬ ችግኞችን ለመትከል ዝግጅት መደረጉን አቶ ትልቅሰው ተናግረዋል፡፡
ዛሬ እየተካሄደ በሚገኘው የችግኝ ተከላ መርኃ ግብር 251 ሺህ 624 ችግኞችን ለመትከል እቅድ ተይዟል ብለዋል፡፡
የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ድረስ ሳኅሉ ( ዶ.ር) “በህልውና ዘመቻው በግንባር ጠላታችንን ከመፋለም ባለፈ ድህነትን ለማሸነፍም ችግኝ መትከል ይገባል” ብለዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ሕዝብም የጁንታው ጥቃት ለመመከት ጠንክሮ እየሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ምክትል ከንቲባው የአረንጓዴ ልማት ሥራውም ሳይስተጓጎል ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የገለጹት፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየከተማቸውን ሰላም በመጠበቅ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እያከናወኑ መሆናቸውን የኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
Next article“የትህነግ ርዝራዦች ኢትዮጵያን ለማዋረድ የሚያደርጉትን ጥረት ለመቀልበስ በቁጭት ተነሳስተናል” አቶ ደስታ ሌዳሞ