
የከተማቸውን ሰላም በመጠበቅ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር እያከናወኑ መሆናቸውን የኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 08/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ለህልውና ዘመቻው የተለያዩ ድጋፎችን በማከናወን ላይ የሚገኙት የኮምቦልቻ ከተማ ነዋሪዎች ለአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም የድርሻቸውን እየተወጡ ነው። ነዋሪዎቹ የአረንጓደ አሻራ መርሃ ግብሩን ያከናወኑት በከተማዋ የተለያዩ ቀበሌዎች ነው።
አሚኮ በተገኘበት ቀበሌ 07 በተከናወነው የአረንጓዴ አሻራ ሥራም የመንግሥና መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማት ሠራተኞች፣ የከተማዋ ነዋሪዎች እና የጸጥታ አካላት ተሳትፈዋል። በዚህም ከ40 ሺህ በላይ ችግኞች ተተክለዋል፡፡
ዛሬ በኮምቦልቻ ከተማ እየተከናወነ በሚገኘው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም ከ93 ሺህ በላይ ችግኞች በተለያዩ የከተማዋ ቀበሌዎች መተከላቸውን የግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊው አቶ ጀማል መሀመድ ገልጸዋል፡፡
የከተማዋ ነዋሪዎች የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን ከማከናወን ባለፈም በአደረጃጀት የአካባቢያቸውን ሰላም እየጠበቁ መሆኑን ለአሚኮ ተናግረዋል፡፡
ነዋሪዎቹ ለህልውና ዘመቻውም አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ወደ ተግባር መግባታቸውንም ጠቅሰዋል።
የኮምቦልቻ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር አህመድ የሱፍ ኀብረተሰቡ የከተማዋን ሰላም ከመጠበቅ ባለፈ ለህልውና ዘመቻው ድጋፍ እያደረገ መኾኑን አስረድተዋል፡፡
የከተማዋ ማኀበረሰብ የአረንጓዴ አሻራ ሥራውን እየከወነ የአካባቢውን ሰላም ለመጠበቅ ከጸጥታ ኀይሉ ጋር በመቀናጀት የጀመረውን ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ሀያት መኮነን-ከኮምቦልቻ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ