በአንድነት በመቆም በአሸባሪው ትህነግ ላይ የማያዳግም እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ ኮሎኔል አለበል አማረ ገለጹ፡፡

295
በአንድነት በመቆም በአሸባሪው ትህነግ ላይ የማያዳግም እርምጃ መውሰድ እንደሚገባ ኮሎኔል አለበል አማረ ገለጹ፡፡
ባሕር ዳር: ሐምሌ 08/2013 ዓ.ም (አሚኮ)ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ቆይታ ያደረጉት ኮሎኔል አለበል አማረ አሸባሪው ትህነግ በተሳሰተ መንገድ የትግራይን ሕዝብ አነሳስቶ ምንም የማያውቁ ሴቶች፣ ሕጻናት እና ሽማግሌዎች አሰልፎ የቆየ የወረራ ፍላጎቱን ለማሳካት በአማራ ክልል ላይ ትንኮሳ መፈጸሙን ጠቅሰዋል፡፡
አሸባሪው ትህነግ እንቅስቃሴ በፍጥነት መቀልበስ አለበት ነው ያሉት፡፡
በሕዝብ ትብብርና በመንግሥት ቆራጥ አመራር ነገሮች እንደሚስተካከሉም ያላቸውን እምነት ገልጸዋል፡፡
አሸባሪው ትህነግ ለአማራ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ እድገት ማነቆ እንደሆነ ኮሎኔል አለበል አስገንዝበዋል፡፡ ዘረኛ እና ጎጠኛው ትህነግ እስካልጠፋ ድረስ ጦሱ ለሁሉም አካባቢ የሚደርስ እንደሆነም ነው ያስረዱት፡፡
የአማራ ክልል ለትግራይ ክልል አዋሳኝ በመሆኑ በኃይል ነጥቀው ይዘውት የቆዩትን የአማራ ግዛት አሁንም ለመውሰድ መሯሯጣቸው ስለማይቀር ሁኔታውን ማምከን እና እንደማይሳካላቸው ማሳዬት ይጠበቃል ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል መንግሥት የሕልውና የትግል ጥሪ ማድረጉን ያነሱት ኮሎኔል አለበል ከአማራ ሕዝብም አልፎ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ትክክለኛውን አቋም እንዲይዙና አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ ማቅረቡን ነው ያነሱት፡፡ በተለያዬ አካባቢ የሚገኘው የአማራ ሕዝብና መላው ኢትዮጵያዊ ጥሪውን ተቀብሎ አስፈላጊውን ዝግጅትና ድጋፍ እያደረጉ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡ ድጋፉ ተጠናክሮ መቀጠል አለበትም ብለዋል፡፡
አሸባሪው ትህነግ የአማራን ግዛት መውረር የማያስችለው አቅም እስኪደርስ ድረስ የሕዝባችን ትብብር፣ ቅንጅትና እንቅስቃሴ፣ የመንግሥት በሳል አመራር ተጠናክሮ መቀጠል አለበትም ብለዋል፡፡
አሸባሪው ትህነግ የውንብድና ተግባርን ተጠቅሞ እስከመጣ ድረስ ተመጣጣኝ የሆነ ኃይል ማዘጋጀትና ሁኔታውን ማክሸፍ እንደሚገባም ኮሎኔሉ ገልጸዋል፡፡ ይህን ለማድረግ ደግሞ ክልሉ የውትድርና ሙያ ያለው ወጣት፣ በሳል የሆኑ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች እንዳሉት ነው የተናገሩት፡፡
በክልሉ በወትድርና ሙያ ልምድ ያላቸው ኃይሎች በአስቸኳይ ከትተው ሚሊሻውና ልዩ ኃይሉን አጠናክረው ሌላውንም ኃይል አስተባብረው ወረራውን መመከት አለባቸው ብለዋል፡፡
ኮሎኔል አለበል የተቃጣውን ወረራ በአጭር ጊዜ ለመቀልበስ የሚያስችል ሥራ እንደሚሠራ ያላቸውን እምነትም ተናግረዋል፡፡
አሸባሪው ትህነግ የተለያዩ የሽብር ቡድኖችን ሰርጎ በማስገባት ሽብር ለመፍጠር እየተንቀሳቀሰ ስለመሆኑም ኮሎኔል አለበል ገልጸዋል፡፡ ዘመኑ ያፈራቸውን መገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም ያላገኘውን ነገር “አገኘሁ”፣ ያላደረገውን ነገር “አደረኩ” እያለ ኅብረሰተቡ ላይ የሥነ ልቦና ጫና ለመፍጠር እያሰበ መሆኑንም አንስተዋል፡፡ ሕዝቡም የአሸባሪውን ትህነግ እና የሌሎች ጠላቶች ሴራ መሆኑን አውቆ ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነቱን መጠበቅና ማስጠበቅ አለበት ብለዋል፡፡
“ጉዳዩ የሕልውና ነው” ያሉት ኮሎኔል አለበል የሚመረጥ አማራ የለም፣ አማራ አማራ ነው፣ የሕልውና አደጋ ውስጥ የሚወድቅበት ስለሚሆን አንድ ኾኖ መነሳት፣ የመንግሥትን ውሳኔዎች፣ አቋሞችና ትዕዛዞች መስማት፣ ማክበርና አስፈላጊ የሆነውን ድጋፍ ማድረግ መቻል አለበትም ነው ያሉት፡፡
ሌሎች ኢትዮጵያውያንም ትግሉን መቀላቀልና የአማራ ሕዝብና መንግሥት እያደረገ ያለውን አቋም መደግፍ እንዳለባቸውም ኮሎኔል አለበል ጠቅሰዋል፡፡
“የአሸባሪው ትህነግ ጉዳይ የሽብርና የውንብድና ጉዳይ ነው፤ ውንብድናውና ሽብርተኝነቱ በአማራ ሕዝብ ብቻ ታጥሮ የሚቀመጥ ሳይሆን ከአማራ ሕዝብ አልፎ ሌላውን ሕዝብ የሚያጠቃ ጉዳይ ነው፤ ሁሉም መተባበርና በአንድ መቆም አለበት፤ ይህን አሸባሪ ቡድን ሳናጠፋ ምንም አይነት ነገር ለመፈጸምና ለመሥራት አንችልም” ነው ያሉት ኮሎኔሉ፡፡
ኮሎኔል አለበል እንደተናገሩት አሁን ላይ አንድነታችን በጣም ያስፈልጋል፤ የፖለቲካ ኃይሎች በጉዳዩ ላይ አንድ ኾነው ትኩረታቸውን በአሸባሪው ቡድን ላይ ማድረግ ይገባቸዋል፤ መረባረብ ከተቻለ የወያኔ ጉዳይ የአንድ ሳምንት ጉዳይ ነውም ብለዋል፡፡
ቀዳዳዎችን በመድፈን መንቀሳቀስ እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሠሩ የምርምርና የፈጠራ ሥራዎች ወደ ተግባር እንዲቀየሩ የሚያደርግ ሥርዓት ተቋማቱ መዘርጋት ይጠበቅባቸዋል” ዶክተር አሕመዲን መሐመድ
Next article“የትህነግ ጁንታ ቡድን ህፃናትን ለሽብር ተግባር ከፊት ማሰለፉ አሳዛኝ ድርጊት ነው” አና ጎሜዝ