
የመንግሥትን ጥሪ ተቀብለው ወደ ትግል ለመቀላቀል መወሰናቸውን በአብርሐጅራ የሚገኙ የቀድሞው የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ተናገሩ።
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 08/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የክልሉ መንግሥት በቅርቡ በሰጠው መግለጫ የቀድሞ የመከላከያ ሠራዊት አባላትን ወደ ህልውና ዘመቻው እንዲቀላቀሉ ጥሪ አቅርቧል። ይህንንም ተከትሎ በምዕራብ ጎንደር ዞን ምዕራብ አርማጭሆ ወረዳ አብርሐጅራ ከተማ በአሸባሪው ቡድን በግፍ ከውትድርና የወጡ የቀድሞው የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባል የህልውና ትግሉን ለመቀላቀል በመመዝገብ ላይ ይገኛሉ።
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን በምዝገባ ጣቢያዎች ተገኝቶ ተመዝጋቢ ምልስ የመከላከያ ሠራዊት አባላትን አነጋግሯል።
የቀድሞው የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባል መቶ አለቃ ካሳሁን ወርቁ ለሀገር ህልውና ሲባል በባድሜና ሽራሮ መዋጋታቸውን ተናግረዋል፡፡ ለትግራይ ሕዝብ የመከላከያ ሠራዊት ልዩ ልዩ የልማት ሥራዎችን ማከናወኑን ገልጸዋል። ይሁን እንጅ የበላበትን ወጭት ለረገጠው ስግብግብ ጁንታ ጊዜ የማይሰጠው በመሆኑ ዛሬም እንደትላንቱ ለሀገራቸው ክብር መሰዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆናቸውን ነው የተናገሩት።
ሌላኛው የቀድሞው የመከላከያ ሠራዊት አባል አስር አለቃ ንጉሤ ዳምጠው በበኩላቸው ትላንት የሀገርን ዳር ደንበር ለማስከበር እንደተሰለፉ ሁሉ ዛሬም የትህነግ አሸባሪ ቡድን በአማራ ሕዝብ ላይ ላደረገው ትንኮሳ መልስ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
ሌላው ወታደር ጌታየ ቢተው አማራ ለሀገር የሚሞት ሕዝብ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የሀገርን ህልውና ማስከበር ኩራትም ጀብድም ነው ብለዋል።
የክልሉን የህልውና አደጋ ለመመከትም መስዋእትነት ለመክፈል ቆርጠው መነሳታቸውን ምልስ የመከላከያ አባላቱ ገልጸዋል። መንግሥት በመግለጫው የቀድሞ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ወደ ዘመቻው እንዲገቡ ጥሪ ማቅረቡ እንዳስደሰታቸውም ተናግረዋል።
ዘጋቢ፡- ቴዎድሮስ ደሴ-ከአብርሐጅራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ