ለአሸባሪው ትህነግ ትንኮሳ የማያዳግም ምላሸ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን የማይካድራ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።

269
ለአሸባሪው ትህነግ ትንኮሳ የማያዳግም ምላሸ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን የማይካድራ ከተማ ነዋሪዎች ገለጹ።
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 08/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አማራ ክብሩን ለማስከበር ተዘጋጅቷል፣ ከአያት ቅድመ አያቶቹ በአደራ የተረከባትን ሰንደቅ ዓላማ ለመጠበቅም ክንዱ አይዝልም፣ ሀገር አማን ሲሆን ሞፈርና ቀንበር አዋድዶ ያርሳል፣ አምርቶም ለሀገር ይመግባል። በደል እየደረሰበትም ቢሆን ከወንድምና እህት ሕዝብ ጋር ለመኖር ሲል ይታገሳል፣ በክብሩና በማንነቱ ለመጣ ግን ነፍጥ ያነሳል።
የሀገር ዳር ድንበር ሲጣስና እናት ሀገሩ ክብሯ ሲደፈር ጎራዴ ስሎ፣ ነፍጡን ወልውሎ ከጠላት ጋር ይፋለማል።
የአማራ የሥነ ልቦና ውቅር፣ ባሕል፣ እሴትና ታሪክ ስለ ሀገር አርቆ ማሰብ፣ ለሀገሩ መሞት፣ ተከባብሮ በእኩልነት መኖር ነው።
አማራ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ጋር ተሰልፎ የሀገሩን ልዕልና ያስከበረ፣ ለሰንደቅ ዓላማው የተዋደቀ ኢትዮጵያን ስመ ገናና ያደረገ፣ የስልጣኔ መሠረትን የጣለ ነው።
ይሁን እንጂ ፍርደ ገምድል ዓለም አቀፍ ተቋማት፣ ኢትዮጵያን ለማዳከም ሌት ከቀን የሚጥሩ ሀገራት እና የሀገር ውስጥ የፋሽስት ውላጅ ባንዳዎች ባይሳካላቸውም የሕዝቡን ክብር ዝቅ ለማድረግና ሥነ ልቦናውን ለማዳከም ብዙ ጥረዋል። ከኢትዮጵያውያን ለመነጠልም ያለግብሩ ግብር ሰጥተው ያላሴሩት ሴራ፣ ያልፈጸሙት ድርጊት የለም።
አሸባሪው ትህነግ የአማራ ሕዝብ ታሪካዊ ጠላት መሆኑን በተግባር አሳይቷል፣ መነሻውም መድረሻውም በአማራ ጠል ትርክት ላይ የተመሠረተ ነውና።
የሀገሪቱን ስልጣን በተቆጣጠረባቸው ዓመታት በሰብዓዊ ፍጥረት ላይ ሊፈጸም የማይገባውን፣ በዓለም ታይቶ የማይታወቅ ግፍና በደል በአማራ ሕዝብ ላይ ፈጽሟል።
በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን ሕዝብ ላይ የተፈጸመው ወሰን አልባ ግፍና በደል ደግሞ ለዚህ አንዱ ማሳያ ነው። ሰዎች ያለማንነታቸው ማንነት ተሰጥቷቸው፣ በቋንቋቸው እንዳይዳኙ፣ ባሕላቸውንም እንዳያሳድጉ ተደርገዋል።
ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ተከትለው ጥያቄ ቢያነሱም ተገደሉ፣ ታሰሩ፣ ታፍነው ደብዛቸው እንዲጠፋ ተደረጉ።
ሽንፈትን የማይቀበሉት የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ አማራዎች ማንነታቸውን ለማስከበርም ከ41 ዓመታት በላይ ታግለው በኀይል የተነፈጋቸውን ነጻነት አስከብረዋል።
ባሰበው መንገድ እንደማይቀጥል የተረዳው አሸባሪው የትህነግ ቡድንም ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ተንኩሶ ኢትዮጵያውያንን ከዳር እሰከ ዳር አስቆጣ። በተወሰደበት አጸፋዊ እርምጃ ጥቅምት 30/2013 ዓ.ም በማይካድራ ከተማ በጥቁር መዝገብ የሰፈረውን እና ታሪክ የማይረሳውን ጅምላ ጭፍጨፋም ፈጽሟል።
በዚህ ድርጊቱም ለአማራ ሕዝብ ያለውን የጥላቻ ጥግ አሳይቷል።
ሕዝቡ ግን በዘመናት ትግሉ በከፈለው መስዋእትነት ከጭቆና ቀንበር ራሱን ነጻ አድርጓል፣ በቋንቋው የመናገር መብቱንም አስጠብቋል።
አሸባሪው የትህነግ ስብስብ ጥቁር ጠባሳ ጥሎ ቢያልፍም አሁን ላይ ማይካድራ ፍጹም ሰላም ሆናለች፣ ነዋሪዎቿም አካባቢያቸውን እየጠበቁ ወደ ልማት ገብተዋል።
የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን የጋዜጠኞች ቡድን በከተማው እንደተመለከተው በርካታ የእርሻ ትራክተሮች እንዲሁም ሠራተኞች ወደ ማሳ ገብተዋል። የፌዴራል ፖሊስ፣ መከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኀይልና ሚሊሻ የአካባቢውን አስተማማኝ ሰላም ለማረጋገጥ በስምሪት ላይ ናቸው።
ይሁን እንጂ የአሸባሪው ቡድን ርዝራዦች በማይካድራ የፈጸሙትን ግፍ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አይኑን ጨፍኖ እንዳላዬ፣ ጆሮውን ደፍኖም እንዳልሰማ ማለፉ ነዋሪዎችን አሳዝኗል። ለአሸባሪው ቡድን ወግኖ እንደተበደሉ ተደርጎ ዓለም አቀፍ መነጋገሪያ ማድረግ ተገቢነት የለውም ብለዋል አስተያየት ሰጪዎች።
ለዚህም መንግሥት ጠንካራ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ሥራ እንደሚጠበቅበት፣ መገናኛ ብዙኀንም እውነታውን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ማስገንዘብ እንዳለባቸው ነው ነዋሪዎቹ የተናገሩት።
ከሰሞኑ የኢትዮጵያ መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔ ማሳለፉን ተከትሎ የአሸባሪው ቡድን አባላት በአማራ ሕዝብ ላይ ሂሳብ እናወራርዳለን ማለታቸው ይታወሳል። ነዋሪዎቹ በሰጡት አስተያዬት ግን ለአሸባሪው ትህነግ የማያዳግም የአጸፋ መልስ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
የወልቃይት ጠገዴ ሕዝብ ዳግም ለጭቆና አይጋለጥም ያሉት አስተያዬት ሰጪዎቹ አካባቢያችንን እያለማን ለሀገራችን ዘብ እንቆማለንም ብለዋል። በመስዋእትነት የተገኘውን ሕዝባዊ ነጻነት ለማስቀጠል የሚጠበቅባቸውን ሁሉ እንደሚወጡም ነው የተናገሩት።
ዘጋቢ:- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየሀገርን ሰላም ለማስከበር የተንቀሳቀሰው የሲዳማ ክልል ልዩ ኃይል ሽኝት እየተደረገለት ነው።
Next articleየመንግሥትን ጥሪ ተቀብለው ወደ ትግል ለመቀላቀል መወሰናቸውን በአብርሐጅራ የሚገኙ የቀድሞው የሀገር መከላከያ ሠራዊት አባላት ተናገሩ።