
“ክልሉ የያዘው አቋም ፍትሐዊ እስከሆነ ድረስ ለፍትሕ የሚከፈል ዋጋ ሁሉ ይከፈላል” የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደኅንነት አማካሪ ገዱ አንዳርጋቸው
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 07/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የፌዴራል እና የአማራ ክልል የሥራ ኀላፊዎች በወቅታዊ ጉዳይ ዙሪያ ከወልድያ ከተማ ነዋሪዎች ጋር ውይይት አድርገዋል። በውይይቱ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደኅንነት አማካሪ ገዱ አንዳርጋቸው፣ የአማራ ክልል መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ኀላፊ አቶ ደሳለኝ ወዳጆ እና የዞኑ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
የሰሜን ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ወልደተንሳይ መኮንን፣ አሸባሪው የትህነግ ቡድን ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በመከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት ከፈጸመበት ጊዜ አንስቶ የዞኑ ሕዝብ ጦርነት ላይ ቆይቷል ብለዋል። በዚህ ወቅትም አሸባሪው ትህነግ በዞኑ ሕዝብ ላይ የፈጸመውን ወረራ ለመቀልበስ የአካባቢውን የጸጥታ ኀይል እና ሕዝቡን በማጠናከር የመከላከል ሥራ መሠራቱንም አብራርተዋል።
ማኅበረሰቡም ከዚህ በፊት የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግ እንደቆየ ኹሉ አሁንም እያደረገ መሆኑን አንስተዋል። አሁንም አሸባሪው ቡድን በአማራ ሕዝብ ላይ እየፈጸመ ያለውን ጥቃት ለመከላል ማኅበረሰቡ መደራጀት እንዳለበት ተናግረዋል። ድጋፉንም አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደኅንነት አማካሪ ገዱ አንዳርጋቸው አሸባሪው ትህነግ ሀገሪቱን ሲመራ በነበረበት ወቅትም በኢትዮጵያ በእኩልነት እና በመከባበር ላይ የተመሠረተ ግንኙነት እንዲኖር፣ ፍትሐዊ የሆነ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት እንዲፈጠር፣ የአማራ የማንነት ጥያቄ የሚነሳባቸው አካባቢዎች መፍትሔ እንዲያገኝ የአማራ ሕዝብና መንግሥት ሲታገል እንደነበር አስታውሰዋል።
በኢትዮጵያ ላይ እንዱ አዛዥ አንዱ ታዛዥ ሆኖ የሀገርን አንድነት ማስቀጠል እንደማይቻል ክልሉ ሲታገል እንደነበር ያስታወሱት አቶ ገዱ የሌሎችን ሀሳብ የማይቀበለው አሸባሪው ትህነግ ግን ሀገሪቱን አሁን ለምትገኝበት ችግር እንዳበቃት አስረድተዋል።
አቶ ገዱ “ክልሉ የያዘው አቋም ፍትሐዊ እስከሆነ ድረስ ለፍትሕ የሚከፈል ዋጋ ኹሉ ይከፈላል፤ ሕጋዊ መንገድንና የሕዝብን ጥያቄ መሠረት ያደረገ ትግል ሁሌም ለውጤት ያደርሳል” ብለዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች አሸባሪው ትህነግ አማራን በጠላትነት ፈርጆ በሌሎች ሀገሪቱ ተንቀሳቅሶ አንዳይሠራ ማድረጉን ተናግረዋል። በሕግ ማስከበር ዘመቻ የሰሜን ወሎ ሕዝብ ለጸጥታ ኀይሉ ደጀን እንደሆነው አሁንም ደጀን ከመሆን ባለፈ ግንባር በመሰለፉ መስዋእት ለመክፈል መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
የትህነግን ጥቃት ለመመከት የክልሉ የሥራ ኀላፊዎች እና ሕዝቡ ወቅቱን የጠበቀ ተግባር መሥራት እንደሚገባቸውም ተሳታፊዎቹ ጠቁመዋል።
በመከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት የፈጸመ ኀይል የሀገር ጠላት እንጂ የአማራ ጠላት ብቻ ባለመሆኑ የፌዴራል መንግሥት እስከመጨረሻው እርምጃ መውሰድ እንደሚገባውም ጠይቀዋል።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ