“መከላከያ ሠራዊቱ መስዋእትነት ከፍሎ የኢትዮጵያን ህልውና ለመታደግ እየሠራ ነው” ሌተናል ጀኔራል ባጫ ደበሌ

585

“መከላከያ ሠራዊቱ መስዋእትነት ከፍሎ የኢትዮጵያን ህልውና ለመታደግ እየሠራ ነው” ሌተናል ጀኔራል ባጫ ደበሌ

ባሕር ዳር: ሐምሌ 07/2013 ዓ.ም (አሚኮ)የኢትዮጵያ መንግሥት በትግራይ ክልል የተናጠል ተኩስ አቁም ውሳኔ ማድረጉ ይታወቃል፡፡ ነገር ግን አሸባሪው የትህነግ ቡድን የተፈጠረውን አጋጣሚ ተጠቅሞ ሕዝቡ አርሶ እንዲበላ እድል ከመስጠት ይልቅ ለሌላ መጠነ ሰፊ ግጭት እያንቀሳቀሰው መሆኑን የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የግንባታ ሥራዎች ዋና አስተባባሪ ሌተናል ጀኔራል ባጫ ደበሌ በሰጡት መግለጫ ገልጸዋል፡፡

ሌተናል ጀኔራል ባጫ እንዳስታወቁት አሸባሪው ቡድን የተናጠል የተኩስ አቁም ስምምነቱን ያልተቀበለው ከቅራኔ እና ግጭት ውጭ ህልውና ስለማይኖረው ነው ብለዋል፡፡ መንግሥት የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔ ሲያሳልፍ ታሳቢ ያደረገው ሕዝቡ የእርሻ ጊዜ እንዲያገኝ አስቦ እንደነበርም አስታውሰዋል፡፡

ነገር ግን አሸባሪው ቡድን ሰላም ባህሪው ባለመሆኑ እና የትግራይ ሕዝብ የእፎይታ ጊዜ ካገኘ ሽማግሌዎቹን አስቀምጦ ወጣቶቹን ወደ ጦርነት ማግዶ የበርካቶቹን ሕይዎት እንዲቀጠፍ በማድረጉ የትግራይ ሕዝብ ነገ እንደሚጠይቀው ያውቃል ያሉት ሌተናል ጀነራሉ ነገ የሚፈጠረው የትግራይ ሕዝብ ጥያቄ የህልውናው ማክተሚያ እና መቀበሪያ ሊሆን እንደሚችል በማመኑ ሕዝቡ ረፍት እንዲኖረው አይፈልግም ብለዋል፡፡

መንግሥት ለትግራይ ሕዝብ የሰጠው የጥሞና ጊዜ ጫካ ለተወሸቀው ቡድን ምቹ አጋጣሚ በመሆኑ ሕጻናትን ወደ ጦርነት እየማገደ ነው፡፡ ለዚህም ሲባል እና በየአካባቢው የሚፈጥረውን ትንኮሳ ለማስቆም መከላከያ ሠራዊት የተጠና እርምጃ ይወስዳል ነው ያሉት ሌተናል ጀኔራል ባጫ፡፡ የምንወስደው እርምጃ ጦርነት እና በወታደራዊ ሳይንስ የሚመራ በመሆኑ አላስፈላጊ መረጃዎችን አናወጣም ብለዋል፡፡

አሸባሪው ቡድን በጫካ የሚኖር፣ የሚታገልለት ዓላማና ሀገር የሌለው፣ ተጠያቂነት የሌለበት እና ኀላፊነት የማይሰማው በመሆኑ የፈለገውን የውሸት ፕሮፖጋንዳ ሊያሰራጭ ይችላል፡፡ ነገር ግን መከላከያ ሠራዊቱ የሚታገልለት ዓላማ፣ ሀገር፣ ሕዝብ፣ ሉዓላዊነት እና ተጠያቂ በመሆኑ እንቅስቃሴዎቹ የተጠኑ እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሕዝብ የአሸባሪው ቡድን የሐሰት ፕሮፖጋንዳ ሰለባ መሆን እንደሌለበትም ገልጸዋል፡፡

“መከላከያ ሠራዊቱ መስዋእትነት ከፍሎ የኢትዮጵያን ህልውና ለመታደግ እየሠራ ነው” ያሉት ሌተናል ጀኔራል ባጫ የኢትዮጵያ ሕዝብ በቁሳቁስ፣ በሞራል እና በሰው ኃይል የተለመደ ድጋፉን እንዲያደርግም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleአሸባሪው ትህነግ በመንግሥት የተላለፈውን የተናጠል የሰብዓዊ የተኩስ አቁም ውሳኔ ውድቅ በማድረግ ስደተኞች በሰፈሩባቸው አካባቢዎች ሳይቀር አዳዲስ ጥቃቶችን መክፈቱን የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡
Next article“ክልሉ የያዘው አቋም ፍትሐዊ እስከሆነ ድረስ ለፍትሕ የሚከፈል ዋጋ ሁሉ ይከፈላል” የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደኅንነት አማካሪ ገዱ አንዳርጋቸው