ʺለአማራ የሕልውና ትግል ግንባሬን እሰጣለሁ” ኮሎኔል ደሴ ሞላ

470

ʺለአማራ የሕልውና ትግል ግንባሬን እሰጣለሁ” ኮሎኔል ደሴ ሞላ
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 07/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በሀገር መከላከያ ሠራዊት ለ30 ዓመታት ሀገራቸውን አገልግለዋል፡፡ ኢትዮጵያ
በሰጠቻቸው ተልዕኮ ውስጥ በመሳተፍ የተሰጣቸውን ኀላፊነት በሚገባ ፈጽመዋል፡፡ የእናት ሀገር ፍቅር፣ የወገን ክብር ምን
እንደሆነ በሚገባ ያውቃሉ፡፡ ለፍቅርና ለክብር ሲሉ የእድሜያቸው ብዙውን ለሀገራቸውና ለሕዝባቸው ሰጥተዋል፡፡
አሁን ደግሞ በጡረታ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ወጥተው በሌላ መስክ ተሰማርተው ነው የሚኖሩት ኮሎኔል ደሴ ሞላ፡፡
በወቅታዊ ጉዳይ ከአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር በነበራቸው ቆይታ ሽብርተኛው ትህነግ ጠላቴ ከሚላቸው ቀዳሚው የአማራ
ሕዝብና መንግሥት ነው ብለዋል፡፡ ለዚህም አሸባሪው ከአመሰራረቱ ጀምሮ አማራ ጠላቴ ነው ብሎ መነሳቱን ነው ያስታወሱት፡፡
አሸባሪው ትህነግ አማራን የማዳከም፣ የመለያየት እና የማሳደድ ሥራ ሲሠራ መኖሩንም ገልጸዋል፡፡ ትህነግ ለአማራ ሕዝብ ጠላት
ነው ያሉት ኮሎኔል ደሴ ሕዝብ የሕልውና ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ፣ ከልማት እንዲደናቀፍና የሽብር ማዕከል እንዲሆን እየሠራ
ነውም ብለዋል፡፡
አሸባሪው ትህነግ በአማራ ሕዝብና መንግሥት ላይ አደጋ መጣሉንም ገልጸዋል፡፡ ከዋሻ ወጥቶ በአማራ ሕዝብ ላይ የጣለውን
አደጋ ለመመከት የክልሉ መንግሥት እያደረገ ያለውን ተግባር መደገፍ እንደሚገባም መክረዋል፡፡
ትህነግ እንኳን ለአማራ ሕዝብ ለትግራይ ሕዝብም አይበጅም ነው ያሉት ኮሎኔሉ ክፍተት ካገኘ ሕዝብን ሊያሳዝን የሚችል እንደ
ማይካድራ የመጨፍጨፍ ተግባር እንደሚፈጽምም ተናግረዋል፡፡
የአማራ ሕዝብ ትልቅ የህልውና ጥያቄ ውስጥ መግባቱንም ገልጸዋል፡፡ የሽብርተኛው ትህነግ እኩይ ተግባር ለመመከት የክልሉ
የሥራ ኀላፊዎች በየደረጃቸው አንድነት በመፍጠር ቁርጠኛ ሆነው ወደ ሥራ መግባት እንደሚገባቸውም ተናግረዋል፡፡ የሥራ
ኀላፊዎች ቁርጠኛ ሆነው ከተደራጁ በኋላ ሕዝቡን በየደረጃው የማንቃት እና የማደራጀት ሥራ መሥራት ይገባቸዋልም ብለዋል፡፡
የወጣቶች፣ የሚሊሻና የሌሎች አደረጃጀቶችን መፍጠር እንደሚገባም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ወጣቱ የችግሩን አሳሳቢነት
ተረድቶ በሚጠበቅበት ሁሉ ለሕልውና እንዲሰለፍ ማድረግ ይገባልም ነው ያሉት፡፡ “የአማራ ሕዝብ የሕልውና ጥያቄ የሚፈታው
የአማራ ሕዝብ ንቁ ተሳትፎ ሲያደርግ ብቻ ነው” ብለዋል ኮሎኔሉ፡፡
ምሁራን ሚናቸውን እንዲወጡ ያሳሰቡት ኮሎኔል ደሴ ተመላሽ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን በፍጥነት በማደራጀት ከልዩ ኃይሉና
ከሚሊሻው ጋር በማቀናጀት ግዳጅ ውስጥ ማስገባት ይገባልም ብለዋል፡፡
የቀድሞ የሠራዊት አባላት ልምዳቸውንና አቅማቸውን ተጠቅመው በክልሉ ላይ የተደቀነውን አደጋ መመከት እንዳለባቸውም
ተናግረዋል፡፡
የክልሉ መንግሥት ያደረገው ጥሪ ተገቢ መሆኑን ያነሱት ኮሎኔሉ ተመላሽ የሠራዊት አባላት በፍጥነት ተመዝግበው ወደ ግዳጅ
መግባት አለባቸው ነው ያሉት፡፡ በተደረገው ጥሪ መሠረት እሳቸውም ለመቀላቀል መዘጋጀታቸውን ነግረውናል፡፡ ኮሎኔል ደሴ
“በአማራ የሕልውና ትግል ግንባሬን እሰጣለሁ” ነው ያሉት፡፡ ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው የጦር መኮንንኖች ጥሪውን በመቀበል
በፍጥነት እንዲገቡና ራሳቸውን በማደራጀት አደረጃጀቶችን መምራት እንደሚገባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ከተለያዩ የጦር
መኮንንኖች ጋር ከመንግሥት ጎን በመቆም መሥራት በሚገባቸው ዙሪያ እየመከሩ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡ መንግሥትም
ከተመላሽ የሠራዊት አባላት ጋር ውይይት ማድረግ እንደሚገባው ነው ያሳሰቡት፡፡
የህልውና ዘመቻው ስኬታማ እንዲሆን የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ከሕዝቡ እንደሚጠበቅም ገልጸዋል፡፡ መላው የአማራ ሕዝብ
ግንባር ለሚሄደው ሠራዊት ሁሉን አቀፍ እገዛ ማድረግ አለበትም ብለዋል፡፡
አሸባሪው ትህነግ ፕሮፓጋንዳ አብሮት ያደገና እንደ ለምድ ለብሶት የመጣ መሆኑን ኮሎኔል ደሴ አንስተዋል፡፡ “አሁን ላይ
ብሶበታል፤ የአማራን ሕዝብ ውዥንብር በመፍጠር ለማጥቃት የማይሠራው ሥራ የለም፤ የቀሩት ርዝራዦች ከውሸት
አይቆጠቡም፤ በውጭ ሆነው የሚያግዟቸው አሉ፤ ውሸት ይዘውት የመጡትና አብሯቸው ያደገ ነው፤ የአማራ ሕዝብ የተለመደ
ውሸታቸውን አውቆ የራሱን ሥራ ብቻ መሥራት ይገባዋል” ብለዋል፡፡
ሕዝቡ በገንዘብና በቁሳቁስ በመደገፍ፣ ግንባር የሚገኙትን ቦታው ድረስ ሄዶ በማበረታታትና አካባቢውን በንቃት በመጠበቅ
የበኩሉን መወጣት አለበት ነው ያሉት፡፡ ሕዝቡ ደጀን በመሆን ወጣቶች ለሕልውና እንዲታገሉ በማድረግና ለዘመቻ የሄዱትን
ቤተሰቦች በማገዝ ኀላፊነቱን መወጣት አለበት ብለዋል፡፡
አሸባሪው ትህነግ በዓለም አቀፍ ሕግ የተወገዘውን እድሜያቸው ያልደረሱ ታዳጊዎችን ለጦርነት እያሰለፈ መሆኑን ጠቅሰዋል
ኮሎኔሉ፡፡ ለራሱ ሕዝብ ደንታ የሌለው፣ ውጊያ የገቡት ሲያፈገፍጉ ከኋላ የሚገድል፣ ለትግራይ ሕዝብ የማያስብ መሆኑን
ተናግረዋል፡፡
የሚደረግው ትግል ሕዝቡ የሕልውና ዘመቻ መሆኑን አውቆና በክልሉ መንግሥት የቀረበለትን ጥሪ ተቀብሎ ራሱን ለመከላከል
መዘጋጀት ይገባዋልም ብለዋል፡፡ አሸባሪው አቅሙና ትጥቁ ስለሚታወቅ ታምር አይፈጠርም፤ ተመጣጣኝ የሆነ መልስ መስጠት
ይቻላልም ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleበባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር በ34 ሚሊዮን ብር ወጪ የተገነባው ዘመናዊ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ፕሮጀክት ለአገልግሎት በቃ፡፡
Next articleአሸባሪው ትህነግ በመንግሥት የተላለፈውን የተናጠል የሰብዓዊ የተኩስ አቁም ውሳኔ ውድቅ በማድረግ ስደተኞች በሰፈሩባቸው አካባቢዎች ሳይቀር አዳዲስ ጥቃቶችን መክፈቱን የስደተኞችና ከስደት ተመላሾች ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡