
ʺእሻ በሉ ጎበዝ የዚያ ሰው ቤት ያውጋ
ከአንበሳ ጉሮሮ ማን ያወጣል ስጋ”
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 07/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ኃያላኑ ያልቻሉት፣ ትንሾቹ እንድምን ሊገፉት? የራስ ደጀን ተራራን እንደመግፋት፣ እሳተ ገሞራን እንደማጥፋት፣ ውቅያኖስን በጭልፋ እንደመቅዳት ይሆንባቸዋል፡፡ አንድ ሆኖ ተነስቷል፣ ያስቀመጠውን ነፍጥ አንስቷል፣ ሁሉም ተጠራርቷል፡፡ ያመቀው ትዕግሥቱ ሲሟጠጥ፣ ጠላት ሊደፍረው ሲቁነጠነጥ በቃኝ ብሎ ገስግሷል፡፡
ʺስደደኝ እና ከጥጉ ድረስ
አቧራ አልብሸው ቶሎ ልመለስ” እያለ ነው፡፡ በየዘመናቱ የመጣበትን ጠላት እየመታ እናት ሀገሩን ነጻ ያወጣ፣ ክፉን ቀን አሳልፎ መልካም ቀን ያመጣ፣ ጠላትን በቅጡ የሚቀጣ ጀግና ሕዝብ ነው አማራ፡፡ ጠላቶቹ እንደ አሸን ቢበዙ፣ ከማዶ ሆነው ሽብር ቢነዙ አማራ ልቡ አይሸበር፣ ጀግንነቱ አይጠረጠር፡፡ ማን ችሎ ይገፈዋል፣ ማንስ ችሎ አንገት ያስደፋዋል፡፡
አማራን አምርሮ የሚጠላውና የሚፈራው ትህነግ ዳግም አንስራርቶ አማራን ለመውጋት አሰፍስፏል፡፡ በኢትዮጵያ ላይ እንደአሻው ለመሆን ከሁሉ አስቀድሞ አማራን ማጥቃት፣ ከዚያም መላው ኢትዮጵያውያንን በጭቆና መግዛት ዓላማው የሆነው የሽብር ቡድኑ በተለያዩ የአማራ ግዛቶች ላይ ጥቃት ከፍቷል፡፡ በወያኔ የተከፈተውን ጥቃት ለመመከትና አደብ ለማስገዛት የአማራ ጀግኖች ወደ ግንባር እየተመሙ ነው፡፡
ʺተንኮለኛ ምጣድ ከኋላ ኖሮ
ለካስ ጠላት ብቻ ሆኛለሁ ዘንድሮ” እያለ የገባበትን ፣ ክብሩን ዝቅ ለማድረግ የሚጥረውን ጠላት አደብ ያስይዝ ዘንድ ግስጋሴ ላይ ነው፡፡ ማንም ደፍሯት የማያውቀውን ክብሩን፣ ጠላት የማይቀላውጥባትን ሀገሩን ለማስከበር አማራ ተነስቷል፡፡ የአማራውን የሕልውና ትግል ለማንኳሰስና ለመቀልበስ የሚጥሩትን ወዮላችሁ እያላቸው ነው፡፡ ክንዴን አትችሉትም፣ ከተነሳሁ አልቀመጥም፣ ከተኮስኩ አልስትም፣ ድል ሳልይዝ ወደቤት አልመጣም እያላቸው ነው፡፡
ʺለእናት ሀገር መሞት የለውም ኩነኔ
ጠላት ለመደምሰስ ነቃ በል ወገኔ” እያለ ወገኑን እያነቃ፣ አራሹ እንዲያርስ፣ ተኳሹ እንዲተኩስ፣ ነጋዴው እንዲነግድ፣ ወገን ጠባቂው በተጠንቀቅ እንዲጠብቅ እያሳሰበ ነው፡፡ አዎን ለእናት ሀገር መሞት የለውም ኩነኔ፣ ይልቁንስ ክብር፣ የሕዝብ ፍቅር፣ የጀግንነት አክሊል ያሰጣል እንጂ፡፡ አማራን ጠላቶቹ ለዓመታት ነካኩት፣ ትዕግስቱን ተፈታተኑት፣ እንደ ዓለት አጠጠሩት፣ እንደ ብረት አጠነከሩት፣ በእልህ አስነሱት፡፡
ኢትዮጵያ ሆይ ብረሳሽ ይርሳኝ፣ ባላስታውስሽ አስታዋሽ ልጣ፣ ባላስከብርሽ ተፋረጅኝ እያለ የሀገር ጠላት የሆነውን ኃይል በአሻገር ለመመለስ፣ ለመደምሰስ እየገሰገሰ ነው፡፡
ቹቹ አለባቸው ዳገት ያበረታው የአማራው ፍኖት በሚለው መጻሕፋቸው ስለአማራ ሲገልጹ ʺየኢትዮጵያን አንድነት ለማስጠበቅና ኢትዮጵያን ለመገንባት በተደረገው እንቅስቃሴ ውስጥ ዐማራ እና ከዐማራ ሕዝብ የፈለቁት የሀገሪቱ መሪዎች ታላቅ አስተዋፅዖ አድርገዋል፡፡ በየጊዜው ከብሔሩ የፈለቁ ነገሥታትና ታላላቅ ምሁራን በዚሕ በኩል ታሪክ ላይ ተጽፎ የቀረ ገድል ፈጽመዋል፡፡ የራቁትን ትተን በቅርብ ከሚታወሱት ነገሥታት ብንነሳ እንኳን አጼ ቴዎድሮስ ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግና ሀገሪቱን ወደዘመናዊነት ለማሸጋገር እና ከዘመኑ ቴክኖሎጂ ጋር ለማስተዋወቅ ያደረጉት ሙከራ ዘወትር ሲታወስ ይኖራል፡፡ ከሸዋ ዐማራ የፈለቁት አጼ ምኒልክም አጼ ቴዎድሮስ የጀመሩትን አንዲት ኢትዮጵያ የመመሥረትና ሀገሪቱን ወደ ዘመናዊነት ደረጃ የማሸጋገር ሕልማቸውን በተሳካ ሁኔታ ለመፈጸም የተጫወቱት ሚና ዛሬም ሲታወስ ይኖራል” ብለዋል፡፡ አማራ ለጋራ ሀገርና ለጋራ ጥቅም ሲል ነፍጥ ያነሳል፣ አልሞ ይተኩሳል፡፡ ሀገር አንድ ያደርጋል፣ ሕዝብን ያስተሳስራል፡፡
አማራ በታሪኩ አያሌ ጀብዱዎችንና ሀገር የሚያኮራ ታሪክ፣ ሕዝብም የሚመካበት ሥራ ሲሠራ ኖሯል፡፡ አሁንም እየሠራ ይገኛል፡፡ ʺ የዐማራ ሕዝብና በየወቅቱ ከሕዝብና ከመሬቱ የፈለቁት መሪዎች አንዲት ኢትዮጵያን ከመገንባት አንጻር የተጫወቱት ሚና ከፍተኛ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ሀገሪቱን ከውጭ መሪዎች ጠብቆ በማቆዬት ረገድም ታላቅ ገድል ፈጽሟል፡፡
ከእንግሊዝ የውጭ ወራሪ ሀገሩን ለመከላከል ሕይወቱን የሰጠውን አጼ ቴዎድሮስን መጥቀስ አንድ የዐማራን ሕዝብና መሪዎቹን ለሀገራቸው የነበራቸውን ቁርጠኝነት ማሳያ ሆኖ የሚታይ ነው፡፡ ለኢትጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካውያንና ለመላው የዓለም የጥቁር ሕዝብ በሙሉ ኩራት የሆነው የዓድዋ ድል የተመዘገበው መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ የማስተሳሰር ብቃቱን ያሳዩት ዕውቁ መሪ አጼ ምኒልክ የተገኙት ከዚሕ ታላቅ ሕዝብና ምድር መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል” ነው ያሉት፡፡
አዎን አማራ ዛሬም የአባቶቹ ልጅ ነውና የቀደመውን ታሪክ ለማስቀጠል ሌላ ታሪክ ለመሥራት በሕልውናው ላይ የገጠመውን አደጋ ለመቀልበስ ዘመቻ ላይ ነው፡፡
ʺከተኮሰ ማይስት ካመነ ማይከዳ
ይምጣ ያገሬ ልጅ የብረት ግድግዳ” እስከሞት የሚያምን፣ የሚታመን፣ ከተኮሰ የማይስት፣ ለነብሱ የማይሰስት ጀግናው ወያኔን ለመቅጣት፣ አሸባሪን በሀገር ላይ ለማጥፋት ዝግጁ ሆኗል፡፡ ትህነጋዊያን ከአማራ ላይ የምናወራርደው ሂሳብ አለ ይሉታል፡፡ እርሱም በተጠንቀቅ ይጠብቃቸዋል፡፡ ሲመጡም ያቀምሳቸዋል፡፡ የአማራን ግዛት ለመውረር፣ ሕዝብን በውሸት ለማደናገር የሚያደርገውን ጥረትም አይሆንልህም እያለ ነው፡፡
ʺእሻ በሉ ጎበዝ የዚያ ሰው ቤት ያውጋ
ከአንበሳ ጉሮሮ ማን ያወጣል ስጋ” እያላቸው ነው፡፡ አዎን ዝም ብለው ያወራሉ እንጂ ከአንበሳ መንጋጋ የገባውን ማን አውጥቶ ሊወስድና፡፡ እንደ ስጋው ሁሉ ወደ መንጋጋ ይገባል፣ ይደቃል፣ ይጠፋል እንጂ ከአንበሳ መንጋጋ የገባውን መውሰድ፣ ከተራራ ጫፍ ላይ የተሰቀለን ክብር ማውረድ፣ ኩሩን ሕዝብ ማሳደድ የሚታሰብ አይደለም፡፡ እነርሱ ያውሩ እኛ እንሠራለን፡፡
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m