
ጁንታው በአማራ ክልልና አካባቢው እየፈጸመ ያለው የሽብር ተግባር በኢትዮጵያ ላይ የተሰነዘረ ጥቃት በመሆኑ በጋራ እንመክተዋለን ሲሉ የሲዳማ ክልል ወጣቶች አስታወቁ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 07/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ጁንታው በአማራ ክልልና አካባቢው እያደረሰ ያለው ጥቃት በኢትዮጵያ ላይ የተሰነዘረ ጥቃት በመሆኑ በጋራ እንመክተዋለን ሲሉ የሲዳማ ክልል ወጣቶች ገለጹ።
ወጣቶቹ አሸባሪው የትህነግ ርዝራዥ ከሰሞኑ በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች እየፈጸመ ያለውን የሽብር ተግባር አስመልክቶ እንደገለጹት፤ “የአሸባሪው ትህነግ ዒላማ ዜጎችን በመከፋፈል ሀገር ማፍረስ ነው” ብለዋል፡፡
የሐዋሳ ከተማ ነዋሪ ወጣት ሰንበቶ በቀለ እንደተናገረው፤ አሸባሪው የትህነግ ጁንታ በአማራ ክልልና በአካባቢው እያደረሰ ያለው ጥቃት የአንድ ክልል ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ሁላችንንም የሚመለከት ነው ሲል ተናግሯል።
አሸባሪው ትህነግ የተሰጠውን የጥሞና ጊዜ እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የሀገርን ሰላም እያናጋ በመሆኑ እኛ ወጣቶች ጊዜ ሳንሰጥ በሀገር ላይ የተጋረጠውን አደጋ በጋራ ልንመክት ይገባል ብሏል፡፡
ከሸበዲኖ ወረዳ ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ወጣት አበበ ሆቤ በበኩሉ የሀገርን ሉዓላዊነት ማስከበር ከአባቶቻችን የወረስነው ጀግንነት እንጂ በተውሶ ያገኘነው አይደለም ሲል ገልጿል፡፡ የአሸባሪዉ ትህነግ ቡድን ለሰላም የተዘረጋውን የኢትዮጵያ እጅ በመንከስ ንጹሐን ዜጎቻችን ላይ የግፍ ተግባር እየፈጸመ ይገኛል ብሏል፡፡ ስለሆነም ይህንን አጥፊና ለሀገርና ለሕዝባችን የማይበጀውን አሸባሪ በጋራ ለመመከት ጊዜው አሁን ነው ሲል ተናግሯል፡፡
አሸባሪው የትህነግ ቡድን በውሸት ፈጠራው ሀገርን በማተራመስና ለውጭ ኃይላትና ጠላቶቻችን አሳልፎ ሊሰጠን አቅዶ እየሰራ በመሆኑ የውስጥ አንድነታችንን በማጠናከር የጥፋት ሴራውን ማክሸፍ ይጠበቅብናል ሲልም ነው የገለጸው፡፡
የሀገራችንን ህልውና ለማስጠበቅና የሕግ የበላይነትን ለማስከበር መንግሥት ለሚወስዳቸው ማናቸውም እርምጃዎች ደጀን በመሆን የሚጠበቅብንን የዜግነትና ሀገራዊ ኃላፊነት መወጣት አማራጭ የሌለው ጉዳይ እንደሆነም ነው የተናገረው ወጣት አበበ፡፡ ለዚህም አስፈላጊውን ሁሉ መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ መሆኑንም ጭምር ነው የገለጸው፡፡
ወራሪዉና አሸባሪው የትህነግ ቡድን አሁን ላይ በተለይ በአማራ ክልል ላይ የደቀነውን አደጋ በሂደት በሌሎች ክልሎችም ሊፈጥር የማይችልበት ሁኔታ የለም፤ ስለዚህም ይህንን አሸባሪ ጁንታ በጋራ መመከት አለብን ያለው ደግሞ ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ወጣት አስናቀ አየለ ነው፡፡
ወጣት አስናቀ እንዳለው ጁንታው በአሁኑ ወቅት እየፈጸመ ያለው የሽብር ተግባር እንደ ሀገር የተደቀነብን አደጋ መሆኑን ተገንዝበን ጊዜ ሳንሰጥ ይህንን ትልቅ የሀገር ጠላት አሽቀንጥረን ልናስወግደው ይገባል፡፡
መላ ኢትዮጵያውያን በጉልበትም ሆነ በዕውቀት ተባብረን አሸባሪውን የትህነግ ሴራ ልናከሽፍ ይገባልም ማለቱን የዘገበው ኢፕድ ነው፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m
