
አደረጃጀቶችን በመፍጠር ለዘመቻ ህልውና ሁለንተናዊ ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን የአማራ ክልል ሴቶች ህጻናት እና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ አስታወቀ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 07/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው ትህነግ የከፈተውን ጦርነት ለመቀልበስ በክልሉ የተለያዩ ከተሞች
አደረጃጀቶችን በማዋቀር የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የአማራ ክልል ሴቶች ህጻናት እና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ገልጿል።
የጎንደር ከተማ አስተዳደርም ለህልውና ዘመቻው የሚያግዙ ተግባራትን እያከናወነ ነው። የጎንደር ከተማ አስተዳደር ሴቶች
ህፃናትና ወጣቶች ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ወይዘሮ ባንቺዓምላክ መልካሙ አሸባሪው ትህነግ በግፍ ያስተዳድራቸው የነበሩ የአማራ
ክልል አካባቢዎችን አሁንም በግፍ ለመንጠቅ ትንኮሳ እያደረገ መሆኑን አንስተዋል፡፡ ነገር ግን በተባበረ ክንድ ጥቃቱን ለመመከት
እየተሠራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ ወይዘሮ ባንቺዓምላክ በክልል ደረጃ የተዋቀሩት አደረጃጀቶች እስከ ቀበሌ እና ወረዳ ድረስ
ወርደዋል ብለዋል፡፡
አደረጃጀቶችን በመጠቀምም ማኅበረሰቡ የአቅሙን ድጋፍ እያደረገ ነው፤ የተደረጉ ድጋፎችም ገንዘብ ፣ ምግብ እና ምግብ ነክ
ያልሆኑ ቁሳቁስ እንደሆኑ ጠቅሰዋል፡፡
ወደ ግንባር የሄዱ ሚሊሻ አባላትን እርሻ የማረስ፣ ግብዓት የማቅረብ እና ሌሎች ድጋፎች እየተደረጉ መሆኑን ኀላፊዋ ጠቁመዋል፡፡
በመምሪያው ሥር በሚገኙ ወረዳዎች እና ቀበሌዎች የሚገኙ ሴቶች እና ወጣቶች ደም እየለገሱ እና በአካልም ለመሳተፍ
መዘጋጀታቸውን እየገለጹ መሆናቸውን ተገናግረዋል፡፡
የአማራ ክልል ሴቶች፣ ህፃናት እና ወጣቶች ጉዳይ ቢሮ ኀላፊ ወይዘሮ አስናቁ ድረስ ለሕግ ማስከበር ዘመቻው የነበረው ድጋፍና
ተሳትፎ ተጠናክሮ መቀጠሉን አስታውቀዋል፡፡ ሥራውን በውጤታማነት ለመፈጸም የተለያዩ አደረጃጀቶች ተግባራዊ እየተደረጉ
መሆናቸውን ነው ኀላፊዋ የገለጹት፡፡
በዚህም በሴቶች ጉዳይ የሚመራው የዓይነት ሃብት አሰባሳቢ ኮሚቴ የሰበሰበውን ወደ ደረቅ ምግብነት የመቀየሩን ሥራ እየሠራ
ነው ብለዋል፡፡ ሃብት የማሰባሰቡ ሥራ በሁሉም አካባቢዎች የተጀመረ ሲሆን ደረቅ ምግብ በማዘጋጀት ተደራሽ የማድረግ ሥራው
በባሕር ዳር፣ በጎንደር፣ በሰሜን ወሎ ዞኖች እና በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አካባቢዎች ቀድሞ መጀመሩንም ነግረውናል፡፡
ከምግብ ዝግጅት እና አቅርቦቱ ጎን ለጎን ሴቶች የአማራ ክልል ልዩ ኃይል እና ሚሊሻ አባላት ሆነው ለመሳተፍ እየተመዘገቡ
መሆኑንም ኀላፊዋ ጠቁመዋል፡፡ አስፈላጊ የሆኑ ቁሳቁስ በማሰባሰብ በሚፈለገው መንገድ እየተሠራጨ መሆኑንም ነው የነገሩን፡፡
የሕዝብ ደጀንነትን ያገኘ ሠራዊት የማሸነፍ ብቃቱ ከፍተኛ መሆኑን የገለጹት ወይዘሮ አስናቁ ሴቶች ለሠራዊቱ ደጀንነታቸውን
ከማረጋገጥ ባሻገር የዘመቱ ሚሊሻ አባል ቤተሰቦችን የማገዝ እና የመንከባከብ ሥራም እሠሩ ነው ብለዋል፡፡
ወጣቶች እና ሴቶች ምግብ ከማዘጋጀት በተጨማሪ ደም በመለገስ ድጋፍ በማድረግ እየተሳተፉ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ቢሮ ኀላፊዋ እንደ ክልል ሴቶች ከሐምሌ 6/2013 ዓ.ም ጀምሮ በአንድ ማዕከል ሆነው ምግብ የሚያዘጋጁበት እና
የሚያቀርቡበት ሁኔታ ተመቻችቷል ነው ያሉት፡፡ ትህነግ ሀገር የማፍረስ ተግባሩን እስካላቆመ ድረስ ሀገር ለማዳን ሁሉም ሰው
ኀላፊነት ወስዶ መሥራት አንዳለበትም ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m