
“ጁንታው የሰላም መንገድ ሊዋጥለት አልቻለም” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 07/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ለትግራይ ሕዝብ ያለንን ሐሳብ፤ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ያለንን ቦታ ለመጨረሻ ጊዜ አሳይተናል። ግጭት ላለማባባስ፣ ለሕዝቡ የእርሻ ወቅት ፋታ ለመስጠት እንዲሁም የርዳታ አቅርቦቱ ያለ ሰበብ እንዲከናወን ስንል በሰብአዊነት ላይ የተመሠረተ የተናጠል የተኩስ አቁም አድርገናል። ሰላም የተወሰነ ዋጋ እንደሚያስከፍለን ብናውቅም ይህ ግን የመጨረሻ ሰላማዊ ዕድል ነው ብለዋል።
ድመት መንኩሳ አመሏን አትረሳ እንደሚባለው ጁንታው የሰላም መንገድ ሊዋጥለት አልቻለም። አሁን ባለው ቁመናው ያለ ግጭት ውሎ ማደር አይችልም ነው ያሉት።
ሕጻናትና ወጣቶችን በአደንዛዥ ዕጽ እያሳበደ ወደ ጦርነት እየማገደ ይገኛል፤ የመከላከያ ሠራዊቱ እነዚህን ሕጻናት ወታደሮች የመታደግ ሞራላዊ ግዴታ ወድቆበታል ብለዋል።
ለሕዝባችን ስንል የከፈልነው ዋጋ ባልገባቸው ደካሞች ምክንያት ውጤት አላመጣም፤ ጁንታው የኢትዮጵያ ህልውና ቀንደኛ ጠላት መሆኑን ደግሞ እያስመሰከረ እንደሆነ ገልጸዋል።
ይሄንንም መላ ሕዝባችንን አስተባብረን እንቀለብሰዋለን። በአንድ በኩል ሰብአዊ ርዳታ እንዲቀላጠፍ እየሠራን በሌላ በኩል የውጭና የውስጥ ጠላቶች ተናበው የከፈቱብንን ጥቃት መክተን እንቀለብሰዋለን ነው ያሉት።
ጁንታው ዋሻ ውስጥ ገብቶ ሕዝቡ በረሐብ ሊያልቅ ነው እያለ ሲያላዝን ነበር። ለሕዝቡ ሲባል ሰብአዊ የተኩስ አቁም ሲደረግ ደግሞ የረሐቡን አጀንዳ ትቶ የጦርነት ነጋሪት መጎሰም መጀመሩን ገልጸዋል።
ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ስለ ርዳታና ስለ ረሐብ ሲናገር መቆየቱን ዘንግቶ ጁንታው ሕጻናትን ሲያሰልፍ እንኳን ዝምታን መርጧል፤ የርዳታ መግቢያ ኮሪደሮችን የግጭት ቦታዎች ሲያደርጋቸው የርዳታ ድርጅቶች አሁንም መንግሥትን ለመውቀስ ይቃጣቸዋል፤ እነዚህን ሁሉ ከግምት በማስገባት መንግሥት አስፈላጊውን ሁሉ ነገር በተገቢው መንገድ ያደርጋል ብለዋል።
ሕዝባችን ከሐሰተኛ መረጃዎች እና ከጠላት ፕሮፓጋንዳ ራሱን እንዲጠብቅ አሁንም ለማሳሰብ እንወዳለን። ጁንታውና አጋሮቹ ያላቸው ዐቅም ውሸትን መፈብረክ ብቻ ነውና። የውስጥና የውጭ ኃይሎች ፕሮፓጋንዳቸውን አቀናጅተው ሕዝብን ለመከፋፈል እየሠሩ ነው። ለዚህ ደግሞ ሕዝባችን እንደ ከዚህ በፊቱ ሁሉ እንደ አንድ ሠራዊት ሆኖ ለሀገሩ ህልውና በመቆም፣ የመከላከያ ሠራዊቱን በሁሉም ነገር በመደገፍ፣ የውጪውን ጫና እና የውስጡን ትንኮሳ እንዲመክትና እንዲቀለብስ ጥሪ እናቀርባለን ነው ያሉት።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ