“የአማራ ሕዝብ ለወደደው ማር ለጠላው ደግሞ ኮሶ ነው” የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ አስተዳዳሪ አሸተ ደምለው

292
“የአማራ ሕዝብ ለወደደው ማር ለጠላው ደግሞ ኮሶ ነው” የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ አስተዳዳሪ አሸተ ደምለው
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 06/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በሑመራ ከተማ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች አሸባሪው ህወሃትን አውግዘዋል። አሸባሪው ቡድን በስማቸው ለፈጸመው በደልም ይቅርታ ጠይቀዋል።
በወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን ሑመራ ከተማ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች አሸባሪው ሕወሃትን በመቃወምና ቡድኑ በኢትዮጵያውያን ላይ ላደረሰው በደል ይቅርታ ለመጠየቅ ዛሬ ሰላማዊ ሰልፍ አካሂደዋል። በሰልፉም አሸባሪው ቡድን በንጹኃን የአማራ ተወላጆች ላይ ያደረሰውን ጭፍጭፋ አውግዘዋል።
አስተያየታቸውን የሰጡ ሰልፈኞች ከሁሉም በላይ ሀገርን ማስቀደም ይገባል ብለዋል። የትግራይ ሕዝብ እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች መኾኑን በማንሳትም “አሸባሪው የትህነግ ቡድን በስማችን ለፈጸመው ግፍና መከራ እኛ ይቅርታ እንጠይቃለን” ብለዋል። ቡድኑን የሚደግፉ አካላት ካሉ ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ እንደሚገባም ሰልፈኞቹ አሳስበዋል።
ሰልፈኞቹ ካሰሟቸው መፈክሮች መካከል “በትግራይ ክልል የሚገኙ የትግሬ ተወላጆች የመከላከያ ደጀን ባለመኾናቸው አዝነናል። ትርፍ የሚገኘው ከአብሮነት እንጂ ከመነጠል አይደለም። የአማራ ሕዝብ አቃፊ እንጂ ገፊ አለመኾኑን አሸባሪው ሳይኾን እኛ እናውቃለን። ትህነግ ጸረ ልማትና ጸረ ሕዝብ ነው። የአማራ ሕዝብ ወንድማችን እንጂ ጠላታችን አይደለም። አሸባሪው ትህነግ በትግራይ ሕዝብ ስም የሚነግድ እንጂ ለትግራይ ሕዝብ ደንታ ቢስ ነው። እኛ በአማራ ክልል የምንገኝ የትግራይ ሕዝብ የማይካድራን ጅምላ ጭፍጨፋ እናወግዛለን። በሱዳንና በትግራይ የምትኖሩ የትግራይ ወጣቶች ዓላማ ለሌለው ጁንታ በአደንዛዥ ዕጽ ተመርዛችሁ ውድ ሕይወታችሁን መክፈል ይብቃችሁ።” የሚሉና ሌሎች መፈክሮችንም አሰምተዋል።
የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሑመራ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አሸተ ደምለው በመርሃ ግብሩ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር የአማራ ሕዝብ አርቆ አሳቢና ኢትዮጵያዊነቱን አጥብቆ የሚወድ ነው ብለዋል። ከመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጋር ለዘመናት የኖረ እና አሁንም እየኖረ ያለ መኾኑንም ጠቅሰዋል።
ምንም እንኳን የአማራና የትግራይ ሕዝብ በአብሮነት የኖረ ቢኾንም ላለፉት ዓመታት አሸባሪው የትህነግ ቡድን ሕዝቡን ለመነጣጠል እንደሠራ አስታውቀዋል።በዚህም የአማራ ሕዝብ ብዙ ግፍና በደል ደርሶበታል፣ ኾኖም ግን አሁንም በኢትዮጵያዊነቱ ቀጥሏል፣ ከትግራይ ሕዝብ ጋርም በሰላም እየኖረ ነው ብለዋል።
“የአማራ ሕዝብ ለወደደው ማር ለጠላው ደግሞ ኮሶ ነው” ያሉት አቶ አሸተ በከተማው የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች ለአሸባሪው ቡድን ተባብረው ከአማራ ሕዝብ ጋር እንዳይጋጩም አሳስበዋል። የማይወደውን ነገር አድርገው ሕዝቡን እንዳያስቆጡም አቶ አሸተ መክረዋል። ሕዝብ አብሮ እንዲኖር የማይፈልጉ አካላትን እንዲመክሩና አሳልፈው እንዲሰጡም ጥሪ አቅርበዋል።
አሁን የትግራይ ሕዝብ ከአሸባሪው ትህነግ ጋር ያለውን ትስስር ቆም ብሎ በሚያይበት የጥሞና ጊዜ ላይ ይገኛልም ብለዋል። የተናጠል የተኩስ አቁም ስምምነቱም ለትግራይ ሕዝብ ታስቦ የተወሰነ መኾኑን አስገንዝበዋል።
በዚህ የጥሞና ጊዜ በሀገር ውስጥም ኾነ በውጪ ሀገራት የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች አሸባሪው ቡድን ከኢትዮጵያውያን ሊለያቸው መኾኑን በሚገባ ተረድተው ሊታገሉት እንደሚገባም ነው የተናገሩት።
ህወሃት ኢትዮጵያን የማፈራረስ አቅም የለውም ያሉት አቶ አሸተ ተከዜን የመሻገር ሀሳብ ካለው ወልቃይት መቀበሪያው ይኾናል ብለዋል።
ዘጋቢ:- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“ለእኛ መኖር ደሙን እየለገሰ ለሚገኘው የጸጥታ ኀይል እንኳን ገንዘብ ከገንዘብ በላይ የሚከፈል ዋጋ ለመስጠት ዝግጁ ነን” የቆቦ ነዋሪዎች
Next articleየትህነግ ሽብርተኛ ቡድን የሚፈጽመውን ትንኮሳ ለመከላከል ዝግጅት ማድረጉን የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የሰላምና የሕዝብ ደኅንነት መምሪያ አስታወቀ።