
“ለእኛ መኖር ደሙን እየለገሰ ለሚገኘው የጸጥታ ኀይል እንኳን ገንዘብ ከገንዘብ በላይ የሚከፈል ዋጋ ለመስጠት ዝግጁ ነን” የቆቦ ነዋሪዎች
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 06/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው ትህነግ በደረሰበት ሽንፈት ዛሬም የቆየ ቂሙን ለመወጣት በኢትዮጵያ ሕዝብ በተለይም ደግሞ በአማራ ሕዝብ ላይ ባገኘው አጋጣሚ ሁሉ እየዛተ ይገኛል።
የአማራ ሕዝብም የተደቀነበትን አደጋ ለመመከት በዝግጅት ላይ ይገኛል። የራያ ቆቦ ሕዝብም ግንባር ለተሰለፈው የጸጥታ ኀይል የገንዘብ ድጋፍ እያደረገ ይገኛል።
ድጋፍ ሲያደርጉ ካገኘናቸው ነዋሪዎች መካከል ዓለምነሽ ደርበው እንደገለጹት የአሸባሪው ትህነግ “ሂሳብ እናወራርዳለን” ዛቻን ለመመከት ለተሰለፈው የጸጥታ ኀይል ማኅበረሰቡን በማስተባበር የገንዘብ፣ የምግብ እና የሞራል ድጋፍ እያደረጉ ነው።
ድጋፍ ከማድረግ ባለፈም ወጣቱ አካባቢውን እየጠበቀ መሆኑን ነግረውናል። አስፈላጊ ኾኖ ከተገኘም ግንባር ለመሠለፍ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።
ወጣት ያለው ታደሰ እንዳለው ደግሞ ለህልውና ማስከበር ዘመቻ ለሚሳተፉ የሚሊሻ አባላት የአካባቢውን ማኅበረሰብ በማስተባበር የእርሻ እና ዘር የመዝራት ሥራ እየተሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ወጣቶችን ከወረዳው የጸጥታ መዋቅር ጋር በማቀናጀት የአካባቢውን ሰላም የመጠበቅ ሥራ እየተሠራ ይገኛልም ብለዋል። የአካባቢው ማኅበረሰብም የምግብ እና የሞራል ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ አንስተዋል።
አቶ ዓለሙ አስጌ ማንንም በማንነቱ እንደማይገፉ ፤ ማንም ቢኾን ደግሞ በህልውናቸው ላይ የሚመጣን ኀይል እንደማይታገሱ ገልጸዋል። ማኅበረሰቡም ለጸጥታ መዋቅሩ በቁሳቁስ እና በገንዘብ ድጋፍ እያደረገ መኾኑን አንስተዋል።
ማንኛውንም ነገር ለማድረግ የሚቻለው የሕዝቦች ማንነት ሲከበር በመኾኑ ሀብት ያለው ሀብቱን ጉልበት ያለው ደግሞ በጉልበቱ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባው አስገንዝበዋል።
ከማኅበረሰቡ የተውጣጣ የምግብ፣ የገንዘብ እና የሞራል ድጋፍ ሲደረግም አሚኮ ከቦታው ተመልክቷል ።
“ለእኛ መኖር ደሙን እየለገሰ ለሚገኘው የጸጥታ ኀይል እንኳን ገንዘብ ከገንዘብ በላይ የሚከፈል ዋጋ ለመስጠት ዝግጁ ነን” ብለዋል የቆቦ ነዋሪዎች።
ዘጋቢ፦ ዳግማዊ ተሠራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ