በዓባይ ተፋሰስ ሀገራት መካከል ዘላቂ ሰላም እና የጋራ ተጠቃሚነትን ለማስፈን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ።

161

በዓባይ ተፋሰስ ሀገራት መካከል ዘላቂ ሰላም እና የጋራ ተጠቃሚነትን ለማስፈን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነትን ማጠናከር እንደሚገባ ተገለጸ።

ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 06/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ ላይ በምትገነባው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ዙሪያ ላለፉት 10 ዓመታት ውዝግቦች እና ሽኩቻዎች ሲስተናገዱ ተስተውለዋል፡፡ ለናይል ወንዝ 86 በመቶ የውኃ ድርሻ አበርክቶ ያላት ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ፀጋዋን ተጠቅማ እንዳታለማ ሲፈጠር የነበረው ጫና ከቅኝ ግዛት ውሎች እና አስተሳሰቦች የተቀዱ እንደነበሩም ይነገራል፡፡

ምንም እንኳን የተፋሰሱ ግርጌ ሀገራት በዓባይ ወንዝ የውኃ ድርሻ ላይ ከዚህ ግባ የሚባል ተሳትፎ ባይኖራቸውም አጠቃቀማቸው ግን ሙሉ በሙሉ የሚባል ሆኖ ቆይቷል፡፡ የአስዋን ግድብን ስትገነባ የተፋሰሱን ሀገራት ያላማከረችው ካይሮ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ የምታነሳው ተቃውሞ ምንጩ ስር የሰደደ ስግብግብነት እንደሆነ ይገለጻል፡፡ የዓባይ ውኃ የበላይነት ስሜት በግብጽ እና ሱዳን ለዘመናት ሲዘወር ቆይቷል፡፡ ለዚህ ያበቃቸው ደግሞ ኢትዮጵያን ጨምሮ በዓባይ ውኃ ድርሻ የጎላ ሚና ያላቸው የተፋሰሱ የላይኞቹ ሀገራት ችግር ጭምር መሆኑን የሚጠቅሱ የዘርፉ ተንታኞች አሉ፡፡ ግብጻውያን የዓባይ ውኃ ምንጩ ከግብጽ እንደሆነ ከመናገር አልፈው ውኃው ለእያንዳንዱ ግብጻዊ ደም እንደሆነ እስከመስበክ ደርሰው ነበር፡፡

በአንፃሩ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን የዓባይ ውኃ ምንጮች እነርሱ ቢሆኑም ይህንን ለቀሪው ዓለም በማስረዳት በኩል ግን ድክመቶች ነበሩባቸው፡፡ በየዘመናቱ ኢትዮጵያን የመሩ ነገሥታት እና መንግሥታት በዓባይ ወንዝ ላይ ግድብ እና መሰል የልማት ፕሮጀክቶችን የመገንባት ፍላጎት እንዳላቸው ቢገልጹም ህልማቸው እውን ሳይሆን እስከዚህ ትውልድ ድረስ ዘልቋል፡፡ ኢትዮጵያ በየዘመናቱ በዓባይ ወንዝ ላይ ለመገንባት የተለመቻቸው የልማት ፕሮጀክቶች እውን ካልሆኑባቸው ምክንያቶች ድህነት፣ የግብጽና ሱዳን ሴራ እና በአካባቢው የነበሩ ቅኝ ገዥዎች የፈጠሩት ፖለቲካዊ ሳንካዎች ተጠቃሾች ናቸው፡፡

በርካታ ፈተናዎችን አልፎ እና ተቋቁሞ ኹለተኛ ዙር የውኃ ሙሌት ላይ የሚገኘው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ለዘመናት የኖረውን ኢ-ፍትሐዊ የዓባይ ውኃ አጠቃቀም በመቀየር በኩል የጎላ ሚና እንዳለው እየተጠቀሰ ነው፡፡ ከሰሞኑም ግብጽ እና ሱዳን ኢትዮጵያ ሁለተኛውን ዙር የውኃ ሙሌት ከማካሄዷ በፊት አስገዳጅ ውል እንድትፈርም የጸጥታው ምክር ቤት ጣልቃ ይግባልኝ ሲሉ ያቀረቡት አቤቱታ በኢትዮጵያ የሀሳብ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡ ኢትዮጵያ በዓባይ ውኃ ፍትሐዊ አጠቃቀም ላይ ያሳየችውን የሀሳብ የበላይነት ለማስቀጠል ወደፊት የምታራምደው ሥነ ተግባቦት ምን መልክ ሊኖረው ይገባል ሲል አሚኮ ባለሙያ አነጋግሯል፡፡

ለዘመናት የነበረውን ኢ-ፍትሐዊ የዓባይ ውኃ አጠቃቀም ምንጩ ከሕግ ቅቡልነት ይልቅ የፕሮፖጋንዳ ልሂቅነት ይታይበት ነበር ያሉን በወሎ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት እና ሥነ ተግባቦት ትምህርት ክፍል መምህር አቶ ኢብራሂም ሰይድ ናቸው፡፡ ግብጽ ራሷን የዓባይ ውኃ ምንጭ አድርጋ ከማቅረብ ባለፈ በእያንዳንዱ ግብጻዊ እሳቤ ውስጥ ዓባይ ከደማቸው ጋር እንዲተሳሰር አድርጋ ነበር ይላሉ የሥነ ተግባቦት ምሁሩ፡፡

ይህም ኢ-ፍትሐዊ የነበረውን የዓባይ ውኃ አጠቃቀም ግብጽ ፍትሐዊ እንደሆነ አድርጋ ለማቅረብ እንዲዳዳት አድርጓል ነው ያሉት፡፡ በአንፃሩ ኢትዮጵያ 86 በመቶ የዓባይ ውኃ አበርክቶ እያላት ዓባይን አልምቶ ለመጠቀም ሌሎችን እንድትለምን አድርጓት ነበር ብለዋል፡፡ የሥነ ተግባቦት ምሁሩ በዓባይ ውኃ ዙሪያ በኢትዮጵያውያን ዘንድ አሁን የተፈጠረውን ሕዝባዊ መነቃቃት ማስቀጠል ተገቢ እንደሆነ አስገንዝበዋል፡፡

የተፋሰሱ ሀገራት ተስማምተው በትብብር እንዲሠሩ ለማድረግ በዓባይ ወንዝ ላይ የጋራ መግባባት ላይ መድረስ እንዳለባቸው ነው የሥነ ተግባቦት ምሁሩ የገለጹት፡፡ ከተጠቃሚነት በዘለለ ብዝሃ ሕይዎቱን በመጠበቅ በኩልም ድርሻ እንዲኖራቸው ማድረግ ተገቢ ነው ብለዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት በተለይም ደግሞ ፐብሊክ ዲፕሎማሲ አዋጭ መፍትሔ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ የዓባይ ወንዝ መነሻ አካባቢን፣ የዓባይ ተፋሰስ ሸለቆን፣ የዓባይ ውኃ ጋን የሆኑ ከፍተኛ ቦታዎችን እና ኢትዮጵያ የዓባይ ተፋሰስን ብዝሃ ሕይዎትን ለማልማት የምታደርገውን የአረንጓዴ አሻራ ለተፋሰሱ ሀገራት ዜጎች ማስጎብኘት ይጠበቅባታል ብለዋል፡፡ በሂደትም ሁሉም የተፋሰሱ ሀገራት ቀጣናውን በማልማት በትብብር እንዲሠሩ ማድረግ ተገቢ መሆኑን አቶ ኢብራሂም ጠቁመዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው

ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡

ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq

በዌብሳይት amharaweb.com

በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ

ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m

Previous articleበአሸባሪው የትህነግ ተጠርጣሪ አባላት ላይ በዚህ ሳምንት ክስ እንደሚመሠረት ተገለጸ።
Next articleበኩር ጋዜጣ ሐምሌ 05/2013 ዕትም