
በሕዝብ በተወካዮች ምክር ቤት ያሉትን የአሠራር ክፍተቶች ከወዲሁ ማስተካከል እንደሚገባ ተገለጸ።
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 04/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያሉትን የአሠራር ክፍተቶች ከወዲሁ በመሙላት ለቀጣዩ ፓርላማ ምቹ ሁኔታን መፍጠር እንደሚገባ አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ ተናገሩ።
የምክር ቤቱና የምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በቢሾፍቱ የሁለት ቀናት ምክክር አድርገዋል፡፡
በዚህም የፓርላማ ዲፕሎማሲ፣ የቋሚ ኮሚቴዎች አደረጃጀት፣ የጄንደር ኦዲት እንዲሁም የጥቆማ፣ ቅሬታና አቤቱታ አቀራረብ ሥርዓትን ማዘመን ያስችላሉ የተባሉ የጥናት ሰነዶች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል።
አሁን ያሉት የምክር ቤት አባላት ለቀጣዩ ፓርላማ ልምዳቸውን የሚያጋሩበት መድረክ ቢመቻች፣ ምሁራንን በማማከር መሥራት ቢቻል እንዲሁም የፓርላማ ዲፕሎማሲን በማጠናከር መንግሥት የማይደርስባቸውን ቦታዎች ተደራሽ ለማድረግ ቢሰሩ የሚሉት ምክረ ሀሳቦች ከጥናቱ አቅራቢዎች ቀርበዋል።
ቀደም ሲል በነበረው አሠራር ፓርላማው አስፈጻሚውን በመከታተልና የእርምት እርምጃ መውሰድ ላይ ውስንነቶች እንደነበሩት የጠቆሙት ምክትል አፈ-ጉባኤ ወይዘሮ ሽታዬ ምናለ፤ የጄንደር ኦዲትን በሚመለከት በፖሊሲ የተደገፈ አሠራር ሊኖር እንደሚገባም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በፓርላማ ዲፕሎማሲ፣ በሕግ አወጣጥ፣ ተጠያቂነትን በማረጋገጥ እንዲሁም በውክልና ሥራዎች ላይ የነበሩትን ውስንነቶች መቅረፍ የሚያስችል አሠራር መከተል እንደሚገባ ያሳሰቡት አፈ-ጉባኤ ታገሰ ጫፎ በመድረኩ የቀረቡትን ግብዓቶች ወስደው ጥናቱን እንዲፈትሹት ለባለሙያዎቹ ሀሳብ ማቅረባቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ