የህዳሴ ግድቡ ሠራተኞች ድርድሩ በአፍሪካ ሕብረት እንዲታይ የጸጥታው ምክር ቤት የወሰደው አቋም ተጨማሪ ብርታት እንደሚሆናቸው ገለጹ።

138
የህዳሴ ግድቡ ሠራተኞች ድርድሩ በአፍሪካ ሕብረት እንዲታይ የጸጥታው ምክር ቤት የወሰደው አቋም ተጨማሪ ብርታት እንደሚሆናቸው ገለጹ።
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 04/2013 ዓ.ም (አሚኮ)
“የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ያሳለፈው ውሳኔ የግብጽና የሱዳንን ኢ-ፍትሐዊ አካሄድ ከማሳየት ባለፈ ለሥራችን ተጨማሪ ብርታት ሰጥቶናል” ሲሉ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሠራተኞች ገለጹ።
የአፍሪካ ሀገራት ለችግሮቻቸው አፍሪካዊ መፍትሔን ማስቀደም እንዳለባቸውም ትምህርት የሰጠ ነው ብለዋል።
በቅርቡ በጸጥታው ምክር ቤት በቀረበው የሕዳሴው ግድብ ጉዳይ የሦስትዮሽ ድርድሩ ወደ አፍሪካ ሕብረት እንዲመለስ በምክር ቤቱ አቋም ተይዟል።
የህዳሴ ግድቡ ሠራተኞች እንዳሉት፤ የምክር ቤቱ አቋም ለሥራቸው ተጨማሪ ብርታት ሆኗል።
መድረኩ የግብጽ እና የሱዳን አካሄድ ፍትሐዊነት የጎደለው ስለመሆኑ ለዓለም ያሳየ እንደነበርም አስታውሰዋል።
ከግድቡ ሠራተኞች መካከል አቶ ኃይሉ ካሳዬ እንዳሉት፤ የፕሮጀክቱ ሠራተኞች እስከ ህይወት መስዋዕትነት ጭምር በመክፈል ለግድቡ ስኬት ሌት ተቀን እየሠሩ ነው፡፡
“የጸጥታው ምክር ቤቱ የወሰደው አቋም ለፕሮጀክቱ ሠራተኞች ተጨማሪ ሞራል ሆኗል” ያሉት አቶ ኃይሉ፤ የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ጠንክረው እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል፡፡
አቶ አበበ ተሻገር የተባሉ ሌላው የግድቡ ሠራተኛ በበኩላቸው ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያዊያን ያለመብራት በጨለማ እየኖሩ መሆኑን አስታውሰዋል፡፡
በተለይ ግብጽ እና ሱዳን ይህን እውነታና የኢትዮጵያን የመልማት ፍላጎት ሕዝባቸው እንዲያውቅ ፈጽሞ እንደማይፈልጉም ነው የገለጹት።
“ኢትዮጵያ የዓባይን ውኃ መጠቀም በተመለከተ በየትኛውም መድረክ እውነታውን ይዛ ነው የምትሟገተው” ያሉት አቶ አበበ፤ የጸጥታው ምክር ቤት ውሳኔ አፍሪካዊ ችግሮች በአፍሪካዊያን በራሳቸው እንደሚፈቱ ያስተማረ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ግድቡን ለፍጻሜ ከመብቃት ወደ ኋላ የሚመልስ ነገር እንደማይኖር የተረጋገጠበት መሆኑን ገልጸው፣ “በሠራተኛው ላይ የተፈጠረው መበረታታት እስከ መስዋእትነት ለመክፈል ያነሳሳ ነው” ብለዋል።
“መጀመሪያም የህዳሴው ግድብ ጉዳይ ወደ ጸጥታው ምክር ቤት መሄድ እንደሌለበት ሁሉም የሚረዳው ሃቅ ነው” ያሉት ደግሞ ኮሎኔል ታምሬ ሙሉነህ የተባሉ የፕሮጀክቱ ሠራተኛ ናቸው፡፡
ምክር ቤቱ ጉዳዮን በአፍሪካ ህብረት ለውይይት እንዲቀርብ መወሰኑ በእጅጉ መደሰታቸውን ተናግረዋል።
“በጸጥታው ምክር ቤት የተወሰደው አቋም ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ለችግሮቻው በራሳቸው መፍትሔ መፈለግ እንዳለባቸው ትምህርት የሰጠ ነው” ብለዋል፡፡
በድንበር ተሻጋሪ ወንዝ የኃይል ማመንጫ ግድብ በመገንባት ኢትዮጵያ የመጀመሪያ እንዳልሆነች የገለጹት ኮሎኔል ታምሬ፤ ሃብቷን በማልማት ለመጠቀም እያደረገችው ያለው ጥረት ወትሮም በተለየ ሁኔታ መታየት እንደሌለበት አመላክተዋል።
የውጪም ሆነ የውስጥ ጠላቶችን ጫና ተቋቁሞ መወጣት የሚቻለው በአንድነት ሲቆም መሆኑንም ገልጸዋል።
አቶ መሃሪ አንተነህ የተባሉ ሠራተኛ በበኩላቸው የህዳሴውን ግድብ በመገንባት ትውልዱ የራሱን አኩሪ ታሪክ የሚያስቀምጥበት መሆኑን ተናግረዋል።
የግብጽ እና ሌሎች ሃገራት ስጋትም ኢትዮጵያ ወደ ልማት የምታደርገው ይሄው ጉዞ እንደሆነ አቶ መሃሪ ለኢዜአ ገልጸዋል፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“የሕዳሴ ግድቡ የጥቁር ሕዝቦች ሁለተኛው የነጻነት ፋና ነው፤ አባይ ኀይል ማመንጫ ብቻ አይደለም ሙሉ ነጻነትን ያጎናጽፈናል” ሌተናል ጀኔራል ባጫ ደበሌ
Next articleበሕዝብ በተወካዮች ምክር ቤት ያሉትን የአሠራር ክፍተቶች ከወዲሁ ማስተካከል እንደሚገባ ተገለጸ።