
“የሕዳሴ ግድቡ የጥቁር ሕዝቦች ሁለተኛው የነጻነት ፋና ነው፤ ዓባይ ኀይል ማመንጫ ብቻ አይደለም ሙሉ ነጻነትን ያጎናጽፈናል” ሌተናል ጀኔራል ባጫ ደበሌ
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 04/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአዲስ አበባ ወጣቶች ዛሬ በወቅታዊ ጉዳይ ላይ መክረዋል። በየካ ክፍለ ከተማ የተሰበሰቡት ከ2 ሺህ በላይ ወጣቶች ክብር ለሀገር አንድነት እና አብሮነት ለተሰው ጀግኖች የመከላከያ ሠራዊት በሚል መሪ ሀሳብ ነው ኢትዮጵያ ላይ የሚታዩ ወቅታዊ ችግሮችን በጋራ ለመታገል ያለመ ውይይት ያካሄዱት።
በመርሃ ግብሩ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ይህ ትውልድ ሀገርን ባስቀደመ መልኩ ድምፄን ሀገሬን ለሚመራው አካል እሰጣለሁ ብሎ ታሪካዊ ምርጫ አካሂዷል ብለዋል።
ሀገራችን በብዙ ተግዳሮቶች ውስጥ ሆና ያካሄደችው ምርጫ ብቻ ሳይሆን ሕዝቡ ሉዓላዊነቱን ያረጋገጠበት ፍትሐዊ ምርጫ እንደሆነም ለወጣቶቹ አብራርተዋል።

የሀገር መከላከያ ሠራዊት ለሀገሪቱ መስዋእት እንደከፈለ ሁሉ እናንተ ደግሞ በየማኅበራዊ ሚዲያው የሚሰራጩ የሐሰት ዘመቻዎችን መከላከል አለባችሁ ነው ያሉት ምክትል ከንቲበዋ ለወጣቶቹ።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የአቅም ግንባታ ሥራዎች አስተባባሪ ሌተናል ጀኔራል ባጫ ደበሌ ኢትዮጵያ ማንም ሞኝ ተሰብስቦ የጠፈጠፋት ሀገር አይደለችም፤ ማንም ሊያፈርሳትም አይችልም ብለዋል። ኢትዮጵያን በትነን ታላቋን ትግራይ እንመሠርታለን ብለው ያሰቡት አሸባሪ ቡድኖችም ህልማቸው ተበትኖ እንዲቀር አድርገነዋል ነው ያሉት።
የሕዳሴ ግድቡ የጥቁር ሕዝቦች ሁለተኛው የነጻነት ፋና ነው፤ አባይ ኀይል ማመንጫ ብቻ አይደለም ሙሉ ነጻነትን ያጎናጽፈናል ያሉት ሌተናል ጀኔራል ባጫ መከላከያ ሠራዊት ማንም ጠላት ቢመጣ ሊመክት በሚችል መልኩ ተደራጅቷል ብለዋል።
በወቅታዊ የሀገሪቱ ጉዳይ ላይ ምክክር ያደረጉት የአዲስ አበባ ወጣቶችም መከላከያ ሠራዊትን በሁሉም መንገድ ለማጠናከርና ለማገዝ ዝግጁነታቸውን ገልጸዋል።
ዘጋቢ:–አንዷለም መናን–ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ