የጸጥታ ኀይሉ ለአሸባሪው ትህነግ ትንኮሳ መልስ ለመስጠት በተጠንቀቅ ላይ መሆኑን የአማራ ክልል ፓሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።

387
የጸጥታ ኀይሉ ለአሸባሪው ትህነግ ትንኮሳ መልስ ለመስጠት በተጠንቀቅ ላይ መሆኑን የአማራ ክልል ፓሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
ባሕር ዳር: ሐምሌ 03/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ሕዝብ ከመላው ኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ጋር በፍቅር፣ በመቻቻል በአንድነት የኖረ ሕዝብ መሆኑን የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የሚዲያና ኮምዩኒኬሽን መምሪያ ኀላፊ ኮማንደር መሠረት ደባልቄ ተናግረዋል።
የአማራ ሕዝብ እየተበደለም ቢኾን በፍቅር፣ በሰላም እና በመቻቻል የኖረ ሕዝብ ነው ያሉት ኮማንደር መሠረት አባቶች ያቆዩትን በጋራ የመኖር ባሕል ኢትዮጵያ ጠል ቡድኖች ሊያጠለሹት ቢሹም ሳይሳካላቸው ቀርቷል ወደፊትም አይሳካላቸውም ብለዋል፡፡
አሸባሪው ትህነግ ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ጦርነት አውጆ ቢንቀሳቀስም ሽንፈትን ተከናንቧል፡፡ ይህ አልበቃህ ያለው የትህነግ አሸባሪ ቡድን አሁንም ጦርነት አውጆ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ነው ያሉት፡፡
አሸባሪው ትህነግ የተለመደ ትንኮሳውን ካደረገ ክልሉ የተለያዩ አደረጃጀቶችን በማጠናከር መዘጋጀቱን ገልጸዋል፡፡
አሸባሪው ቡድን መከላከያ ሠራዊቱን አዳክሞ በሕዝብ ትግል ያጣውን የአራት ኪሎ ቤተ መንግሥት እንደገና ለመቆናጠጥ ቢፈልግም የመከላከያ ሠራዊቱ ራሱን አደራጅቶ ባደረገው ተጋድሎ እና የአማራ ክልል ልዩ ኀይል ከአማራ ሚሊሻ ጋር ባደረገው ትግል ዳግም ላይመለስ ተንኮታኩቷል ብለዋል፡፡
አሸባሪው ትህነግ አይቀጡ ቅጣት ቢቀጣም “ያደቆነ ሠይጣን ሳያቀስስ አይለቅም” እንዲሉ በአማራ ሕዝብ ላይ ለዳግም ጥቃት ጦር መስበቁን ይፋ አድርጓል ነው ያሉት፡፡
ኮማንደር መሠረት እንዳሉት አሸባሪው ትህነግ በሥልጣን ዘመኑ የአማራ ክልል አካባቢዎችን ወደ ትግራይ በጉልበት በመከለል ግፉ ሲፈፅም ቆይቷል፤ የአማራ ክልል ሕዝም አካባቢዎቹ ወደ ቀደመ ማንነታቸው እንዲመለሱ ሲጠይቅ አሻፈረኝ ያለው ትህነግ እራሱ በጀመረው ጦርነት ሳይወድ በግዱ የአማራ ልዩ ኀይል ከመከላከያ ሠራዊቱ እና ሚሊሻው ጋር በከፈለው መስዋእትነት ተመልሷል፡፡
አሸባሪው ትህነግ ላለፉት ሦስት አስርት ዓመታት በአማራ ሕዝብ ላይ ያደረሰው ግፍ አልበቃ ብሎት በድጋሜ ሒሳብ ለማወራረድ አሁንም ጦርነት አውጇል ብለዋል፡፡
የአማራ ክልል ልዩ ኀይል እና ሚሊሻ የተቃጣበትን ጦርነት ለመመከትም ራሱን በተገቢው መንገድ አደራጅቷል፤ የሚሊሻ ኀይሉም ለህልውና ዘመቻው ራሱን አዘጋጅቷል ብለዋል።
የጸጥታ ሆነ የፖለቲካ አመራሩም የሚፈለገውን ዝግጅት አድርጎ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ነው ያሉት ኮማንደሯ፡፡
ወደ ግንባር ከዘመተው ኀይል በተጨማሪ መደበኛ ፖሊስ፣ ሚሊሻ እና ልዩ ኀይል ከመቸውም በበለጠ በተጠንቀቅ እየጠበቀ ነውም ብለዋል፡፡
የሀገሩን ዳር ድንበር ለማስከበር ወደ ግንባር የገሰገሰው ሚሊሻ ቤተሰቦቹን ለሕዝቡ አደራ ጥሎ የሄደ በመኾኑ የሚሊሻው ቤተሰቦች ችግር እንዳይገጥማቸው አስፈላጊው እገዛ የሚደረግበት አሠራር መዘርጋቱንም ኮማንደሯ አንስተዋል፡፡
የትህነግ አሻጥሮች የሽብር ተግባር ለመፈጸም የተለያዩ ስልቶችን ቀይሰው ቢንቀሳቀሱም አሁንም ድባቅ እየተመቱ መኾኑን ተናግረዋል፡፡
አማራ አቃፊ ሕዝብ ነው፤ ገፍቶ የማይጣላ፣ በሌሎች ላይ ችግር ለመፍጠር የማይጥር ነገር ግን በአንድነቱ እና በሉዓላዊነቱ የሚመጡበትን ደግሞ የማይታገስ “አራስ ነብር” ማለት ነው ብለዋል ኮማንደሯ፡፡
ማኅበረሰቡ በተለያዩ ሥራዎች ለመከላከያው እና ለአማራ ልዩ ኀይል አጋርነቱን እያረጋገጠ ነው ይህንንም አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ኮማንደር መሠረት አስገንዝበዋል፡፡
ወጣቱም ከአማራ ልዩ ኀይል እና ከመከላከያ ሠራዊት ጎን በመሰለፍ አጋርነቱን እያሳዬ ነው፤ ይሄም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል ኮማንደር መሠረት፡፡
ዘጋቢ፡- ትርንጎ ይፍሩ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6
Previous articleየደረጃ”ሐ” ግብር ከፋዮች የሚጠበቅባቸውን ግብር በተያዘለት ጊዜ ከፍለው ማጠናቀቅ እንዳለባቸው የአማራ ክልል ገቢዎች ቢሮ አሳሰበ።
Next articleየኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ውጤትን ይፋ ማድረጉን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላለፉ።