
“ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መምሕራን የሚያደርጉትን ድጋፍ ለማጠናከር ታቅዷል” የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 03/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የኢትዮጵያ መምህራን ለታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ እያደረጉ ያለውን ድጋፍ አጠናክሮ ለማስቀጠል ማቀዱን ማኅበሩ አስታወቀ።
የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መሰረት ከተጣለበት ጊዜ አንስቶ በማኅበርም ኾነ በግለሰብ ደረጃ የቦንድ ግዥ እንዲካሔድ በመሥራት የበኩሉን አስተዋጽኦ ሲያደርግ መቆየቱም ተገልጿል።
የማኅበሩ ፕሬዚዳንት ዶክተር ዮሐንስ በንቲ እንደተናገሩት፤ ማኅበሩ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ እስኪጠናቀቅ ድረስ ድጋፉን በተጠናከረ መልኩ ለማድረገ የተለያዩ ተግባራትን እያከናወነ ነው። ለአብነትም በተጠናቀቀው ሳምንት የ250 ሺህ ብር የቦንድ ግዥ ፈጽሟል።
ዶክተር ዮሀንስ እንደሚሉት፤ በአዲሱ በጀት ዓመትም የትምህርት ማኅበረሰብ የቦንድ ግዥ እንዲፈጽምና በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥል ለማድረግ የተለያዩ ተግባራት ታቅደዋል።
በአሁኑ ወቅት ከመምህራን ባሻገርም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በራሱ ሀብትና ላብ የጀመረው ግንባታ እንዲጠናቀቅ ለማገዝ ሰፊ ተነሳሽነት እየታየ መሆኑንም አንስተዋል። በመሆኑም መንግሥት ይሕንን እድል በመጠቀም ሃብት የማሰባሰብ ሥራውን በተደራጀ መንገድ መቀጠል አለበት ያሉት ዶክተር ዮሐንስ፤ ለኅብረተሰቡም መረጃዎችን በወቅቱ ማቅረብ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያን የኃይል ፍላጎት በማማሏት በኩል በርካታ ችግሮችን ይፈታል ተብሎ ተስፋ የተጣለበት ፕሮጀክት ዕውን እንዲሆን በቀጣይም ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ነው የተጠቆመው።
በዓለም አቀፍ ደረጃም አሁን እየተካሔዱ ያሉ የዲፕሎማሲ ሥራዎችንም አጠናክሮ የመቀጠልን አስፈላጊነት አጽንኦ የሰጡት ዶክተር ዮሐንሰ፤ የተፋሰሱ ሀገሮች ከታላቁ ህዳሴ ግንባታ የተሻለ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ በማሳወቅ ረገድ ሰፊ ሥራ መሥራት አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመዋል። ኢዜአ እንደዘገበው፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ