“የዛሬው የመጀመሪያ ደረጃ የምርጫ ውጤት መግለጫ ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ሂደት ወሳኝ ምዕራፍ ነው” አምባሳደር ስቴፋን አዎር

121
“የዛሬው የመጀመሪያ ደረጃ የምርጫ ውጤት መግለጫ ለኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ሥርዓት ሂደት ወሳኝ ምዕራፍ ነው” አምባሳደር ስቴፋን አዎር
ባሕር ዳር: ሐምሌ 03/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የስድስተኛው ሀገራዊ ምርጫ የመጀመሪያ ደረጃ ውጤትን አስመልክቶ የምርጫ ቦርድ ውጤት መግለጫ መርኃግብር እየተካሄደ ይገኛል፡፡ በመግለጫው የምርጫ ሂደቱ ስኬታማ እንዲሆን ድጋፍ ያደረጉ የውጭ ድርጅቶች እና ሀገራት ተወካዮች ተገኝተዋል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሪዝደንት አስተባባሪ ሞሪን አቺንግ የኢትዮጵያ መንግሥት በጎርጎሮሳዊያኑ አቆጣጠር 2019 ገደማ ድጋፍ እንዲደረግለት በጠየቀው መሰረት ምርጫን በተመለከተ የሚሠራው ሲድ ኢትዮጵያ ፕሮጀክት እውን መሆኑን አውስተዋል፡፡
ሲድ ኢትዮጵያ ምርጫው ስኬታማ እንዲኾን ቴክኒካል እና ኦፕሬሽናል ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል ያሉት ሞሪን አቺንግ በመራጮች ትምህርት፣ በቁሳቁስ ግዥ፣ በቴክኖሎጂ በእውቀት ሽግግር እና በፋይናንስ ድጋፍ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡
ሞሪና አቺንግ ድርጅታቸው በቀጣይም ኢትዮጵያ የምታደርገውን የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ በብዙ መንገድ ለመደገፍ ቁርጠኛ ነው ብለዋል፡፡
በውስጣዊ ግጭቶች፣ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እና በሌሎች ችግሮች መካከል የተደረገው ምርጫ ሰላማዊ ኾኖ መጠናቀቁ አስደሳች ነበር ያሉት ደግሞ የጀርመን አምባሳደር ስቴፋን አዎር ናቸው፡፡
አምባሳደር ስቴፋን በምርጫው ዕለት በርካታ ኢትዮጵያውያን ለመምረጥና ዲሞከራሲያዊ መብታቸውን በሰላማዊ መንገድ ለመጠቀም በመቻላቸው ሊመሰገኑ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ምርጫ ሁልጊዜም ቀላል ሂደት አይደለም፤ አልፎ አልፎ ያልተጠበቁ ክስተቶች እና የተለየ አመለካከት ያላቸው አካላት ሂደቱን አስቸጋሪ ያደርጉታል ነው ያሉት፡፡ ይህንን ሁሉ ችግሮች ተቋቁሞ ሰላማዊ እና አሳታፊ ምርጫ ማካሄድ ፈተናው ብዙ ነው ብለዋል፡፡ አምባሳደሩ “ሰላማዊ የምርጫ ሂደት እንዲለመድ የመሰረት ድንጋይ ለጣለው የምርጫ ቦርድ ምስጋና ይገባል” ብለዋል፡፡
ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ መንግሥት እና የምርጫው ባለቤት የኾነውን የኢትዮጵያ ሕዝብ የጀርመንን ሕዝብና መንግሥት ወክየ እንኳን ደስ አላችሁ ማለት እፈልጋለሁ ብለዋል፡፡ በዚህ ምርጫ የፋይናንስ እና የቴክኒክ ድጋፍ ያደረገችው ጀርመን በውጤታማ ምርጫችሁ ለነበራት ተሳትፎ ኩራት ይሰማታል ነው ያሉት አምባሳደሩ በመልዕክታቸው፡፡
ዘጋቢ፡- ታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleየኢትዮጵያ ሲቪክ ማኅበራት ሕብረት በሰው ኀይል እና በቴክኖሎጂ ራሱን በማጠናከር የማኅበረሰብ አገልግልት እንደሚሰጥ ገለጸ፡፡
Next article“በትልቅ ሀገር ውስጥ ውስን ሎጂስቲክስ ይዞ ምርጫ ማከናውን ከባድ ቢሆንም መፍትሔ ማምጣትና ማረም የሚችሉ ባለሙያዎች በመኖራቸው ስድስተኛው ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫን በስኬት ማከናውን ተችሏል” የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ብርቱካን ሚዴቅሳ