
ከቀያቸው የተፈናቀሉ ወገኖች በዘላቂነት እስኪቋቋሙ ድረስ የሚደረገው ሰብዓዊ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለጸ፡፡
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 03/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በመተከል ዞን ተፈጥሮ በነበረው ግጭት ከቀያቸው የተፈናቀሉ ወገኖች በዘላቂነት
እስኪቋቋሙ ድረስ የሚደረገው ሰብዓዊ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የዞኑ ኮማንድ ፖስት ገለጸ።
በመተከል ዞን የተቀናጀ ግብረኃይል ኮማንድ ፖስት የተመራ ልዑክ ከአማራ እና ቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች፣ ከመተከል ዞንና
ከየወረዳዎች የተውጣጡ የሥራ ኃላፊዎች በአራት የወረዳ ማዕከላት የሚገኙ ተፈናቃይ ወገኖችን ጎብኝተዋል።
በጉብኝቱ ወቅት በሁሉም ማዕከላት የሚገኙ ወገኖች እንደ ምግብ፣ ውኃ፣ ፍራሽ፣ አልባሳት እንዲሟሉላቸው፣ የህክምና፣
የመድኃኒት አቅርቦት እንዲጨመርላቸው፣ ሌሎች የሰብዓዊ ድጋፎች በሰዓቱ እንዲደርሳቸው ጠይቀዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊትና ሌሎች የጸጥታ አካላት ደኅንነታቸውን ለመጠበቅ እያደረጉት ላለው አስተማማኝ ጥበቃም ምስጋና
አቅርበዋል።
በዞንና ወረዳ ደረጃ የተጀመረው የእርቀ ሰላም ሂደት እስከቀበሌ ድረስ ወርዶ ወደ ቀያቸው የሚመለሱበት ሁኔታ እንዲመቻችና
መደበኛ ህይወታቸውን እንዲመሩ ተፈናቃዮቹ ጠይቀዋል።
የዞኑ ኮማንድ ፖስት ሰብሳቢ ሌተናል ጄኔራል አስራት ዴኔሮ እንደተናገሩት፤ መንግሥት በዞኑ የተለያዩ የወረዳ ቀበሌዎች ተፈጥሮ
በነበረ ግጭት የተፈናቀሉ ወገኖች በዘላቂነት እስኪቋቋሙ ድረስ የሚያደርገውን ሰብዓዊ ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል።
የዞኑ ኮማንድ ፖስቱና መንግሥት የተፈናቀሉ ወገኖችን በዘላቂነት እስኪቋቋሙ ከዞን እስከቀበሌ ድረስ እርቀ ሰላም እንዲወርድ
በማድረግ ወደ የመኖሪያ ቀያቸው ለመመለስ በጋራ እየሠሩ መሆኑን አመልክተዋል።
የምዕራብ እዝ ምክትል አዛዥ እና የኮማንድ ፖስቱ አባል ብርጋዴር ጀኔራል ዓለማየሁ ወልዴ በበኩላቸው፤ ድጋፉ ለሚመለከተው
አካል እንዳይደርስ በተፈናቃይ ስም የሚያጭበረብሩ አካላትን በማጋለጥ ተጠያቂ እንዲሆኑ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
በየማዕከላቱ የሚገኙ ዜጎችን ደኅንነት ለመጠበቅም ሠራዊቱ በሙሉ አቅሙ እየሠራ እንደሚገኝም ተናግረዋል።
የመተከል ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ጋሹ ዱጋዝ፤ በየማዕከሉ የሚገኙ ዜጎችን ደኅንነት ለመጠበቅ የሀገር መከላከያ ሠራዊትና
ሌሎች የጸጥታ አካላት ሙሉ ኃላፊነት ወስደው እየሠሩ መሆኑን ገልጸዋል።
የሰብዓዊ ድጋፍ ለማሟላት በመጓጓዝ ሂደት ላይ መሆኑን ተገልጿል፤ በየማዕከላቱ እንደደረሱም በአስቸኳይ እንዲሰራጭ
እንደሚደረግ ተጠቁሟል።
የህክምና አገልግሎት፣ የአልባሳት፣ የድንኳን ማነስ እና ሌሎች የመገልገያ ቁሳቁሶች እጥረቶች እንደሚሟሉም በወቅቱ ተገልጿል።
ኢዜአ እንደዘገበው፡፡
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m