
በደቡብ ጎንደር ዞን ካለው አጠቃላይ የጎርፍ አደጋ ተጋላጭነት አንጻር 80 በመቶ ገደማ የሚሆነውን ሥራ ለማከናወን ተጨማሪ
ሀብትና ሰፊ ሥራ እንደሚያስፈልግ የዞኑ አስተዳደር ገለጸ፡፡
ባሕር ዳር: ሐምሌ 03/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በደቡብ ጎንደር ዞን በተለይም በፎገራ፣ በሊቦ ከምከምና በደራ ወረዳዎች
በሚከሰት የጎርፍ አደጋ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለተደጋጋሚ ሰብዓዊ፣ ማኅበራዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ ችግሮች ተጋልጠዋል፡፡
በተለይ በባለፈው ዓመት የክረምት ወቅት በተከሰተ ጎርፍ ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ቀለመወርቅ ምህረቴ
አስታውሰዋል፡፡ በተደጋጋሚ የጎርፍ አደጋ መከሰቱን ተከትሎም ክረምት በገባ ቁጥር ሰዎች ለስነልቦና ችግር መጋለጣቸውን ነው
የተናገሩት፡፡
እንደ ዋና አስተዳዳሪው ገለጻ በዓመት ሦስት ጊዜ ማምረት የሚችሉ አካባቢዎች በጎርፍ መከሰት ምክንያት አንደኛው የሰብል
ወቅት ያለ ምርት ያልፋል፡፡ አርሶ አደሮች በለም መሬት ላይ እየኖሩ የመከላከል ሥራ ባለመከናወኑ ማግኘት የሚገባቸውን ሀብት
አጥተዋል፡፡
ባለፈው ዓመት በክልሉ አቅም ችግሩን ለመቀነስ በተከናወኑ ተግባራት በክረምት ሰብል ተዘርቶባቸው የማያውቁ አካባቢዎች
ታርሰዋል፣ ጥሩ ምርት እንደተገኘባቸውም አስታውቀዋል፡፡
ባለፈው በጀት ዓመት ደግሞ የተሻለ ሥራ ተሠርቷል ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ ዞኑ ካለው በጎርፍ የመጠቃት ችግር አንጻር የተሠራው
20 በመቶ ያህሉ ነው፡፡ ቀሪ 80 በመቶ ገደማ የሚሆነው ተጨማሪ ሀብትና ሰፊ ሥራ እንደሚያስፈልገው ነው አቶ ቀለመወርቅ
የተናገሩት፡፡
የፌዴራል መንግሥት ችግሩን በባለቤትነት ወስዶ እየሠራ ይገኛል፤ በቀጣይም በቂ ጊዜና ገንዘብ ተይዞለት እንደሚሠራ
አስታውቀዋል፡፡
ከክልሉ ውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ልማት ቢሮ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው ከ21 ኪሎሜትር በላይ የቦይ ከፈታን የማሳደግና
ማስፋት እንዲሁም ደለል የማውጣት ሥራ ተከናውኗል፡፡ ይህም በበጀት ዓመቱ ለመሥራት ከታቀደው 75 በመቶ ገደማ ነው፡፡
የቢሮው ኀላፊ ማማሩ አያሌው (ዶክተር) ሥራው በተከናወነባቸው አካባቢዎች በጎርፍ አደጋ ምክንያት የሚፈጠር መፈናቀልን
በ80 በመቶ ገደማ መቀነስ ተችሏል ብለዋል፡፡ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የረዥም ጊዜ እቅድ እንደተያዘለትም አንስተዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m