
አሸባሪውና ከሐዲው የትህነግ ቡድን የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላት መሆኑን በመረዳት ሁሉም የሽብር ቡድኑን ድርጊት የማጥፋት እርምጃ ላይ በአጋርነት መቆም እንዳለበት አቶ አብርሃም አለኸኝ ጥሪ አቀረቡ።
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 03/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የአማራ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ አብርሃም አለኸኝ ከአሚኮ ጋር ቆይታ አድርገዋል።
ስድስተኛው አጠቃላይ ምርጫ ካለብን ውስጣዊና ውጫዊ ስጋት አንጻር ሲመዘን ውጤታማና እንደ ሀገር ሁላችንም አሸናፊዎች የሆንበት ክስተት ነው ብለዋል። ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጤናማ የትግል ስልትንና አማራጭ ሐሳባችንን አስቀድመን ለሕዝብ አሳውቀናል፤ ሕዝቡም በነጻነት ለሀገር ይበጃል የሚለውን መምረጡን ተናግረዋል፡፡
አሸባሪው ትህነግ የኢትዮጵያዊያንና ኢትዮጵያዊነት ክብርና አንድነት የማይገደው ለስልጣን ቆይታው ብቻ የሚመቸውን ሴራ በመጎንጎን የሚታወቅ መሆኑን አንስተዋል አቶ አብርሃም።
ወልቃይት ጠገዴና ራያ በኃይል ባስተዳደረባቸው ዓመታት አማራን ለማጥፋት ያልፈጸመው ግፍና በደል የለም ያሉት አቶ አብርሃም ሕዝቡም የአማራነት ክብሩን ለማስከበር መጠነ ሰፊ መስዋእትነት ከፍሏል ብለዋል።
ሽብርተኛው ትህነግ የጥፋት ጥጉን በተግባር ባሳዬበት የሰሜን እዝ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ጥቃት ቅጽበት በቅራቅርና ሶሮቃ የአማራን ሕዝብ በመውረርና በማጥቃት ወደ መሀል ሀገር የመግባት የቅዠት ህልሙ በጀግናው የአማራ ልዩ ኀይልና ሚሊሻ አከርካሪው ተበጥሶ መንኮታኮቱን ጠቅሰዋል።
አሸባሪው ትህነግ በአደባባይ የአማራን ሕዝብ ጠላቴ ነው ይበል እንጅ መላ የኢትዮጵያን ህዝብ በዝብዟል፤ አዋርዷል፤ ብሔራዊ ክብራችን ዝቅ እንዲል ያላደረገው ጥረት የለም ሲሉም የጥፋት ትግበራውን አብራርተዋል።
ከምስረታው ጀምሮ የአማራን ሕዝብ በጠላትነት በመፈረጅ አሁንም በሞት አፋፍ ላይ ኾኖ በተደጋጋሚ ሒሳብ አወራርዳለሁ የሚለው የቆዬ ምግባሩ አይሳካለትም ነው ያሉት።
በአማራ ሕዝብ ላይ አወራርደዋለሁ የሚለው ሒሳብም የረጅም ዓመታት የጭፍን ጥላቻ ማሳያው ነው፤ ይህ አዲስ ክስተት አይደለም ያሉት አቶ አብርሃም ይልቁንም ሽብርተኛው ትህነግ በአማራና በኢትዮጵያ ሕዝብ የፈጸመው ዘርፈ ብዙ በደል ባለእዳ ነው ብለውታል።
የአማራ ሕዝብ በህልውናው የመጣበትን በመመከት አሳፍሮ በመላክ የጥንት የአባቶቹ ታሪክ በግልጽ ይናገራል፤ አሁንም የሽብርተኛውን ቡድን ጥቃት ለመመከት ዝግጁ ነን ብለዋል። “በሕዝባችንም ሙሉ እምነት አለን፤ ኩራትም ይሰማናል ነው” ያሉት።
አሸባሪውና ከሐዲው የትህነግ ቡድን የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላት መሆኑን በመረዳት ሁሉም የሽብር ቡድኑን ድርጊት የማጥፋት እርምጃ ላይ በአጋርነት መቆም እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል።
ተፎካካሪ ፓርቲዎች ምርጫ ከሀገር ህልውና በታች መሆኑን በመረዳት የኢትዮጵያን ውስጣዊና ውጫዊ ችግር ለመፍታት በትብብርና በአንድነት መቆም እንደሚገባም አስገንዝበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ስማቸው እሸቴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m