
“የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን ለማጠናቀቅ ከመቼውም ጊዜ በተለየ ሁኔታ በተቀናጀ መንገድ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል” ዶክተር አረጋዊ በርሔ
ባሕር ዳር: ሐምሌ 02/2013 ዓ.ም (አሚኮ)የኢትዮጵያ ታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ለማጠናቀቅ ከመቼውም ጊዜ በተለየ ሁኔታ በተደራጀና በተቀናጀ መንገድ መንቀሳቀስ እንደሚገባ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
የጸጥታው ምክር ቤት የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ የተፋሰሱ ሀገራት በአፍሪካ ሕብረት አማካኝነት መቀጠል እንደሚገባ መግለጹ ተገቢ መሆኑንም ገልጿል።
የጽሕፈት ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አረጋዊ በርሔ እንደተናገሩት በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለግድቡ ግንባታ ከኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን 16 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ ገንዘብ ማሰባሰብ ተችሏል።
የዲያስፖራው ማኅበረሰብ ለግድቡ ግንባታ እያደረገ ያለው ተሳትፎ መጨመሩንም ነው የገለጹት።
በ2013 ዓ.ም ብቻ ዲያስፖራው ለግድቡ ግንባታ አንድ ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ማዋጣቱንም ለአብነት ጠቅሰዋል።
የግድቡ የሁለተኛ ዙር የውኃ ሙሊት እየተከናወነ መሆኑ ለኢትዮጵያውያን ብስራት መሆኑን ጠቅሰው፤ በውጭ ሀገርም ኾነ በሀገር ውስጥ ያሉ ኢትዮጵያውያን ከመቼውም ጊዜ በተለየ መልኩ የግድቡን ግንባታ ለማጠናቀቅ በተቀናጀ መንገድ መንቀሳቀስ አለባቸው ነው ያሉት።
ኢትዮጵያውያን ከግድቡ ባሻገር የሀገር ጥቅምን ለማስጠበቅ በቅንጅት መሥራት እንዳለባቸውም ጥሪ አቅርበዋል።
ምክር ቤቱ ኢትዮጵያውያን በተደራጀ መንገድ ተሳትፎ የሚያደርጉበት ትስስር መፍጠሩንም ገልጸዋል።
ግብጽና ሱዳን ለዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ የተሳሳተ መረጃ በመስጠት ኢትዮጵያ ተገቢ ድጋፍ እንዳታገኝ ተጽእኖ ሲያደርጉ መቆየታቸውንም አስታውሰዋል።
በኢትዮጵያ መንግሥት፣ በዲፕሎማቶችና ዳያስፖራዎች ይህን ተጽእኖ ለመመከት በርካታ ሥራዎች ሲያከናውኑ መቆየታቸውን አስታውሰው፤ ይህም የጸጥታው ምክር ቤት የግድቡ ድርድር በአፍሪካ ሕብረት በኩል እንዲሆን ድጋፍ ለማድረጉ አዎንታዊ ሚና መጫወቱን ነው ያመለከቱት።
የጸጥታው ምክር ቤት ድርድሩ በአፍሪካ ሕብረት እንዲታይ ያሳየው ድጋፍ ዲፕሎማሲያዊ ድል መሆኑንም ዶክተር አረጋዊ መግለጻቸውን የዘገበው ኢዜአ ነው።
የግድቡ ውኃ ሙሊት ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በ2015 የደረሱበትን የስምምነት መርሆች ባከበረ መልኩ እየተከናወነ መሆኑንም አስገንዝበዋል። በመሆኑ የተፋሰሱ ሀገራት ላይ ጉዳት እንደማያደርስ የሚታወቅ መሆኑን ተናግረዋል።
ትናንት በተካሔደው የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ የውኃ፣ መስኖ ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ “የታላቁ ሕዳሴ ግድብ በሁሉም ኢትዮጵያዊ ደም፣ ላብና እንባ የሚገነባ ነው” ሲሉ መግለጻቸው ይታወሳል።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6