የጎርፍ አደጋን ለመቀነስ የተከናወኑ ተግባራት በአደጋው የሚፈጠር መፈናቀልን ከ80 እስከ 90 በመቶ እንደሚቀንሱ ተገለጸ፡፡

173

የጎርፍ አደጋን ለመቀነስ የተከናወኑ ተግባራት በአደጋው የሚፈጠር መፈናቀልን ከ80 እስከ 90 በመቶ እንደሚቀንሱ ተገለጸ፡፡
ባሕር ዳር: ሐምሌ 02/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በባለፈው ዓመት የክረምት ወቅት እንደ ሀገር በተከሰተ የጎርፍ አደጋ ከ1 ሚሊዮን
በላይ ሰዎች ተፈናቅለዋል፤ ከ300 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ ለከፋ ችግር ተጋልጠዋል፡፡
በተያዘው ዓመት አደጋው እንዳይከሰት መንግሥት በትኩረት እየሠራ መኾኑን የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የርብና ጉማራ ወንዝ አካባቢዎች በጎርፍ እንዳይጠቁ የፌዴራል መንግሥት ቅድሚያ ሰጥቷቸዋል፡፡ በክረምቱ ሊፈጠር የሚችል
የጎርፍ አደጋን ለመቀነስ የክትር ሥራ፣ የደለል ጠረጋ፣ ቦይ የማስፋትና ጥልቀት እንዲኖረው የማድረግ ተግባር እየተከናወነ ነው፡፡
ለዚህ ወደ 240 ሚሊዮን ብር እንደተመደበም ሚኒስቴሩ አስረድቷል፡፡
የፌዴራልና የክልል የሥራ ኀላፊዎች የተከናወኑ ተግባራትን ዛሬ የመስክ ምልከታ አድርጓል፡፡ ተግባራቱ በታቀደው መሠረት
እየተከናወኑ እንደኾነ የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዴኤታ አብርሃ አዱኛ (ዶ.ር) ገልጸዋል፡፡ በጀት ዘግይቶ በመለቀቁ ሥራው
ቀደም ብሎ ባይጀመርም በአጭር ጊዜያት ጥሩ ውጤት መገኘቱን አብራርተዋል፡፡ የፕሮጀክቱ የውል ስምምነት ለ12 ወራት
ስለሚቆይ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አመላክተዋል፡፡
የተፋሰሶች ልማት ባለስልጣን እንዳስታወቀው ችግሮችን መቀነስ በሚያስችል ጥናት ላይ ተመስርቶ ዲዛይን ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ
ተገብቷል፡፡ የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አዳነች ያሬድ (ዶ.ር) እንዳሉት የተሠራው ሥራ የነበረውን መፈናቀል ከ80 እስከ 90
በመቶ ይቀንሳል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡
አንዳንድ አካባቢዎች በቀላሉ ሊሸረሸር የሚችል አፈር መኖሩ ተስተውሏል፡፡ እንዲረጋ የማድረግ ሥራ ግን ተጠናክሮ ይቀጥላል
ብለዋል፡፡ ጅምር ሥራው የአካባቢውን ችግር ሙሉ በሙሉ ስለማይቀርፍ ቀጣይነት ያለው ሥራ ይከናወናል፡፡ ከተሠራው አልፎ
ሊከሰት የሚችል የጎርፍ አደጋ ካለም ቅድመ ትንበያ በመሥራት ሕዝቡን ከጉዳት ለመታደግ ጥረት እንደሚደረግ አመላክተዋል፡፡
የአማራ የክልል ምክትል ርእሰ መስተዳድር ፈንታ ማንደፍሮ (ዶ.ር) የዓባይ እና ጢስ እሳት የግንባታ ተቋራጮች በቂ ማሽን
አስገብተው ውጤታማ ሥራ እየሠሩ እንደኾነ አመላክተዋል፡፡ ክረምቱ ቢገባም ሙሉ በሙሉ ሥራ እስከሚከለክል
እንደሚቀጥልም ተናግረዋል፡፡
የተጀማመሩ ሥራዎች ውጤታማ እንዲኾኑና ጎርፍ የመከላከል ሥራው ዘላቂነት እንዲኖረው ማኅበረሰቡን ያሳተፈ የችግኝ ተከላ
ያስፈልጋል፤ ለጎርፍ ከሚያጋልጡ ሰው ሠራሽ ድርጊቶች መቆጠብ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡
የአካባቢው ነዋሪዎች የጎርፍ አደጋን ለመከላከል የተከናወኑ ተግባራት ስጋታቸውን እንደቀነሰው ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ ክረምቱ
ቀድሞ በመግባቱ ሥራው ሙሉ በሙሉ አለመጠናቀቁን አንስተዋል፡፡ ይህም በተለይ ክረምቱ እንደባለፈው ዓመት የሚከብድ ከኾነ
ችግሩ ዳግም ሊከሰት እንደሚችል ያላቸውን ስጋት ገልጸዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ደጀኔ በቀለ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
ዩቱዩብ https://bit.ly/2RnNHCq
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ

Previous article“የአሸባሪው ህወሃት መኖር ለቀጣናው አለመረጋጋት ምክንያት ይሆናል” የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር
Next article“ኢትዮጵያ እና ኬንያ በሁለት ሀገራት የሚኖሩ አንድ ሕዝቦች ናቸው” የኬንያ ምክትል ፕሬዚደንት