
“የአሸባሪው ህወሃት መኖር ለቀጣናው አለመረጋጋት ምክንያት ይሆናል” የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር
ባሕር ዳር: ሐምሌ 02/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አሸባሪው ህወሃት ከራሱ ክልል አልፎ ለሀገርም ኾነ ዓለም አቀፍ ስጋት እንዳይኾን ኹሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች ርብርብ አድርገው ሊታገሉት እንደሚገባ አሚኮ ያነጋገራቸው የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ተናግረዋል፡፡
በደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ዳምጠው ተሰማ (ረዳት ፕሮፌሰር) አሸባሪው ህወሃት በአደባባይ ሕዝብ ይጨፈጭፋል፣ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ያዘዋውራል፣ ሀገሪቱን የብጥብጥ ማዕከል ለማድረግ የሚሠራ በመኾኑ ጊዜ ከገዛ የዓለም ስጋት የማይኾንበት ምንም አይነት ምክንያት ሊኖር አይችልም ብለዋል፡፡
አሸባሪው ቡድን ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅም በተቃራኒ ከቆሙ ማንኛውም አካላት ጎን የሚሰለፍ ነው ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ አሸባሪው ቡድን በተቻለው አቅም ሁሉ የኢትዮጵያን ጉልበት ለማመንመን ሲሠራ የቆየና እየሠራ የሚገኝ ስብስብ ነው ብለዋል፡፡
ህወሃት የአማራ ሕዝብን ብቻ ሳይኾን የመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ስጋት እንደኾነም አስረድተዋል፡፡ “የአማራ ሕዝብ ራሱን የመከላከል ብቃት ያለው ቢኾንም ሁሉም የሀገሪቱ ሕዝቦች አንድ ኾነው ሊከላከሉት ይገባል” ብለዋል፡፡
የሰሜን እዝን በመውጋትና በመፈጸምና የአማራን ሕዝብ በማጥቃት ዓላማው ቤተ መንግሥትን መያዝ ነበር ነው ያሉት፡፡ ቤተ መንግሥት ገብቶ ቢኾን ደግሞ ጠላት ያላቸውን ሁሉ በማጥቃት ኢትዮጵያዊያንን ለዳግም ባርነትና ሰቆቃ የማይጥልበት ምክንያት እንደሌለም ነው የተናገሩት፡፡
ህወሃት ከታሪክ እይታ ሲቃኝ ባለፉት 60 ዓመታት የምሥራቅ አፍሪካን ሀገራትን ሰላም ከሚነሱት አካላት ጋር በመኾን ቀጣናውን ከመረበሽ ባሻገር ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውር በስፋት በማካሄድና ኢንቨስትመንቶችን በማሰናከል ይታወቅ እንደነበር ረዳት ፕሮፌሰር ዳምጠው አስረድተዋል፡፡
“የአሸባሪው ህወሃት መኖር ለቀጣናው አለመረጋጋት ምክንያት ይሆናል” ያሉት ረዳት ፕሮፌሰሩ ህወሃት እንደሱ አሸባሪ ቡድኖችን በመፈልፈል በቃጣናውም ኾነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የችግር ምንጭ እንደሚኾን መታወቅ አለበት ብለዋል፡፡
አሁን ላይ ህወሃት መጥፎ አስተሳሰቡን ከመርጨት ውጭ በተደራጀ መልኩ ጥቃት የመፈጸም አቅም የለውምም ብለዋም፡፡ ክፉ አስተሳሰቡ ግን በማኅበረሰቡ ውስጥ የመግባት አቅም ስላለው እንደ ችግር ታይቶ መፍትሔ ያስፈልገዋል ነው ያሉት፡፡
በተበታተነ መንገድ ያለውን የአሸባሪውን የህወሃት አባላት ጨርሶ ለማጥፋት ወታደራዊና ፖለቲካዊ እርምጃ እንደሚያስፈልግ አመላክተዋል፡፡ ህወሃት የሚባለው ቡድን በሽብርተኝነት መፈረጁ የጎላ ጠቀሜታ እንዳለውም ምሁሩ ጠቁመዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ቡሩክ ተሾመ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
ትዊተር https://bit.ly/37m6a4m