
የሀገራቸውን ሰላም ለማስጠበቅ መሰዋእትነት ለመክፈል መዘጋጀታቸውን የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ነዎሪዎች ተናገሩ።
ባሕር ዳር: ሐምሌ 02/2013 ዓ.ም (አሚኮ) ከአሸባሪው ትህነግ ግፍና ጭቆና ነጻ የወጣው የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ሕዝብ አሁን ላይ ሰላማዊ እና ልማታዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ይገኛል።
ከሰሞኑ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ከትግራይ ክልል መውጣቱን ተከትሎ የአሸባሪው ትህነግ ርዝራዦች ከያሉበት ተሰባስበው ወልቃይትን ዳግም እናስመልሳለን በሚል ሲናገሩ ይሰማሉ፡፡ ይሁን እንጅ እነዚህን አሸባሪዎች አይቀጡ ቅጣት ቀጥቶ በመጡበት እንዲመለሱ አሊያም መቀበሪያቸው እዛው እንዲኾን መሰዋእትነት ለመክፈል መዘጋጀታቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡
በሰቲት ሁመራ ከተማ የቀበሌ 02 ነዋሪ የኾነው ወጣት ማርየ ጫኔ “አሸባሪው ህወሃት ወልቃይትና ራያ የኔ ነው የሚለው የህልም ቅዥት ነው” ብሏል፡፡ የወልቃይት ሕዝብም ከመከላከያ ሠራዊት፣ ከአማራ ልዩ ኀይል እና ከአማራ ሚሊሻ ጋር ማንኛውንም መስዋእትነት ለመክፈል ዝግጁ እንደኾኑ ገልጿል፡፡ በወልቃይት እና በራያ ጉዳይ ህይወታቸውን እስከመስጠት ድረስ እንደሚደርሱ ነው የተናገረው፡፡
ወጣት እሰየ ማሞ ላለፉት ሰላሳ ዓመታት የግፍ ጽዋን ስንጋት ነበር፤ በአሸባሪው ትህነግ ከፍተኛ ስቃይን አይተናል፤ ማይካድራ ላይ ተጨፍጭፈናል ይህም ኾኖ ዳግም ላይመለስ ወልቃይት ወደ ማንነቱ አማራ ተመልሷል ብሏል።
አሁንም አሸባሪው ቡድን አላርፍ ካለ መልሰን መላልሰን የወልቃይት አማራ ጀግንነትን በተግባር እናሳያለን ነው ያለው።
ነዎሪዎቹ የእርሻ እና የዘር ወቅት በመሆኑ የአካባቢያቸውን ልማት እያፋጠኑ የሚመጣባቸውን የጠላት ትንኮሳ ለመመከት እና ሰላማቸውን ለማስጠበቅ ዝግጁ እንደኾኑም አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ፡- ያየህ ፈንቴ – ከሁመራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ