ክፍል 2 “ጥቅምት 24” የቀን ክህደት

461
ክፍል 2 “ጥቅምት 24” የቀን ክህደት
ባሕር ዳር: ሐምሌ 02/2013 ዓ.ም (አሚኮ) 2013 አዲስ ዓመት በጠባ ማግስት ኢትዮጵያ ፈታኝ ሀገራዊ እና አህጉራዊ ችግሮች አንዣበውባት ነበር፡፡ የኮሮናቫይረስ አስደንጋጭ ስርጭት፣ የአምበጣ መንጋ ክስተት እና የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ዙር የውኃ ሙሌትን ተከትሎ በግብጽ እና ሱዳን የሚዘወረው የሴራ ጫና ሀገሪቱን ገና በጠዋቱ የቤት ሥራ አብዝቶባት ነበር፡፡
በተለይም የአፋር ክልል አዋሳኝ በኾነባቸው የአማራ እና ትግራይ ክልሎች የተከሰተው የአምበጣ መንጋ የብዙኀንን ቀልብ ስቦ ቆይቷል፡፡ ይባስ ብሎ ደግሞ የሀገሪቱን ሁለንተናዊ መልክ የቀየረው የጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ጥቃት ሀገሪቱን የከፋ የሕልውና አደጋ ውስጥ ከተታት፡፡
ጥቅምት 24 በመላው ትግራይ የቀበሮ ጉድጓድ ውስጥ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ ራሱን ቀብሮ ትግራይን እና ኢትዮጵያን ሲጠብቅ የነበረው የሀገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ገና በጠዋት ለአምበጣ መከላከል በአርሶ አደሩ ማሳ ውስጥ ተሰግስጎ ነበር የዋለው፡፡ መከላከያ ሠራዊት ለትግራይ ሕዝብ ኮቸሮውን አካፍሎ፣ የኮዳ ውኃውን ለግሶ፣ ደመወዙን ለትምህርት ቤት ግንባታ ቀንሶ እና በሰላም ጊዜ አርሶ የድሃውን ሕይዎት አብሮ የኖረ የሕዝብ ልጅ ነው፡፡
ባለፉት ሦስት አስርት ዓመታት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እንደ ትግራይ ሕዝብ ያገለገለው ብሔር ስለመኖሩ አጠራጣሪ ነው፡፡ “ወርቅ ላበደረ ጠጠር…” እንዲሉ ኾኖ ከድካም እንዳረፈ እና ትጥቁን እንደፈታ ወገን በሚለው ከጀርባው ተወጋ፡፡
ክህደት በተጠናዎተው ሴራ ከሰው ልጅ ሰብዓዊ ክብር በእጅጉ በወረደ መልኩ የማይታሰቡ ድርጊቶችን በመፈጸም ያን የክብር ዘብ ከክብር በታች ለማውረድ ሞከሩ፡፡ በዚህ መካከል አብሮ ለመኖር ሲባል የማይነገሩ፣ ለሀገር ክብር ሲባል የማይወሩና ለትግራይ ሕዝብ ሥም ሲባል የማይወጡ በርካታ አስነዋሪ ድርጊቶችም ተፈጽመዋል፡፡
“በግፍ የበለጸገ በግፍ ይደኽያል” እንደሚሉት ኾኖ ህወሃት ከመሪነት ርካብ በወረደ ማግስት ከስብእናም ወርዶ ቀን አርሶ አደር ማሳ ከአምበጣ መንጋ ጋር ሲራወጥ የዋለን ወታደር በተኛበት ገብቶ በመውጋት የሀገር ክህደቱን በግልጽ አሳየ፡፡ 80 በመቶ የሀገሪቱ የጦር መሳሪያ በእጃችን ነው፣ ሰሜን ዕዝ ሙሉ በሙሉ ወድሟል እና ሌሎች ወታደራዊ ሚስጥርን የሚጥሱ መግለጫዎችን በመስጠት ሀገርን ለውጭ ባዕዳን አጋለጧት፡፡ ሱዳን ደንበርን ጥሶ ገብቶ መንሰራፋት ህወሃት ባዘጋጀው ቀዳዳ የመግባታቸው ሚስጥር መኾኑ ለማንም ግልጽ ነበር፡፡ ዳሩ ግን እነርሱ የሚያውቋት ኢትዮጵያ እነርሱ የዘረፏትን እንጅ ወቅታዊዋን ኢትዮጵያን የመገንዘብ አቅሙም ፍላጎቱም አልነበራቸውም፡፡
የአማራ ልዩ ኀይልና ሚሊሻ የተከበቡትን የመከላከያ ሠራዊት አባላት ነፃ አውጥቶ የአሸባሪውን ጉዞ እና ህልም ገታው፡፡ ከመከላከያ ሠራዊት ጥቃት በኋላ አሸባሪዎቹ ቢችሉ ኖሮ ቀጥለው ማንን ሊያጠቁ እንደሚችሉ መገመት ከባድ አልነበረም፡፡ ቁርሳቸውን ጎንደር ምሳ ባሕር ዳር ላይ አዳራቸው ሸገር የታቀደላቸው የህወሃት አሸባሪ ቡድን ጀግናውን የአማራ ልዩ ኀይል፣ ሚሊሻ እና የመከላከያ ክንድ መቋቋም ተስኗቸው ለጊዜውም ቢኾን ከትግራይ ሳይወጡ ተወስነው ቆዩ፡፡
ውሸት አብሯቸው ያደገው፣ ክህደት የተጠናዎታቸው እና አዙሮ ማየትን ያልተካኑት አሸባሪዎቹ በጦርነት አውድ የደረሰባቸውን ጉዳት በምላሳቸው ማካካስ ዋና ሥራቸው አደረጉት፡፡ አይደለም ከጦርነት ርቆ ላለው ማኅበረሰብ ይቅርና በቅርበት ለሚከታተሉት እንኳ በሚያጠራጥር መልኩ ሕዳር 19/2013 ዓ.ም ከመቀሌ ለቆ የወጣው ቡድን ከወልድያ እስከ ሸዋ ከጎንደር እስከ ጎጃም ተቆጣጠርኩ ሲል መስማት አስቂኝ ነበር፡፡
የኾነው ኾኖ መከላከያ በደረሰበት ክህደት ልክ ሳይኾን ሀገርን በሚያድን መልኩ አካባቢውን ሙሉ በሙሉ ለመቆጣጠር የሚያስችል ወታደራዊ ስምሪት ለማድረግ ተዘጋጀ፡፡ ጦርነቱ ቦታ አልበቃ ያላቸው የአሸባሪው ቡድን አባላትን በቀበሮ ዋሻ ውስጥ ይቀረቅራቸው ዘንድ ግድ ኾነ፣ ገሚሶቹ እስከወዲያኛው አሸለቡ ቀሪዎቹም ለካዱት የመከላከያ ኀይል እጅ ለመስጠት ያልከበዳቸው የሥነ ልቦና ባለቤት ኾነው ተገኙና እጃቸውን ሰጡ፡፡
የአማራ ሕዝብ እንደ ሕዝብ የትግራይ ሕዝብ ጠላት ኾኖ ሂሳብ የሚወራረድበት ምንም ምክንያት አልነበረም፡፡ እንዲያውም ነገሩ ይገለጥ ከተባለ በተቃራኒው ኾኖ እናገኘዋለን፡፡ ለዘመናት ማንነቱን ተነጥቆ እና ከቀየው ርቆ እንዲኖር የተገደደው በአሸባሪው የህወሃት አልጠግብ ባይ ስግብግብ ሹማምንቱ እንደነበር እነርሱ ራሳቸው ያውቁታል፡፡ ለፍትሕ፣ ለእኩልነት እና ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የታገሉ ቁርጥ የአማራ ልጆች በርካቶቹ ደብዛቸው ጠፍቷል፣ በግፍ ተገድለዋል፣ ለአካል እና ሥነ ልቦና ስብራት ተጋልጠዋል፡፡ እንዲህም ኾኖ ግን የአማራ ሕዝብ ትግሉ ከሥርዓት ጋር እንጂ ከትግራይ ሕዝብ ጋር ሆኖ አያውቅም፡፡
ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊያንን ለዘመናት ከዓለት አጽንቶ እና ከምሰሶ አበርትቶ ያቆመው የአማራ ሕዝብ ራሱን ለመከላከልም ኾነ ጠላቶቹን አሳድዶ አፈር ለማልበስ ወኔውም ኾነ አቅሙ እንዳለው እነርሱ ራሳቸው ያውቁታል፡፡ አብሮ ለመኖር፣ ለሀገር አንድነት፣ ለመልካም ጉርብትና እና ከሁሉም በላይ ለፍትሕ ከነበረው የማይናዎጥ አቋም ላለመንሸራተት ሲል ለመሸከም ቀርቶ ለመስማት የሚከብዱትን መከራዎች ሁሉ አሳልፎ፣ አሁን ላይ ጠላቶቹን አይቀጡ ቅጣት በመቅጣት ማንነቱን አስመልሶ አማራው ለዳግም ድል ከፊት ተሠልፏል፡፡
በታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበሱዳን የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ለሀገራቸው ልማት የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑ ተገለጸ።
Next articleየሀገራቸውን ሰላም ለማስጠበቅ መሰዋእትነት ለመክፈል መዘጋጀታቸውን የወልቃይት ጠገዴ ሰቲት ሁመራ ነዎሪዎች ተናገሩ።