
በሱዳን የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ለሀገራቸው ልማት የድርሻቸውን እየተወጡ መሆኑ ተገለጸ።
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 02/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በሱዳን የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በሀገሪቱ ያለውን የኑሮ ውድነትና የተለያዩ ችግሮችን በመቋቋም በሀገራቸው የልማትና የሰብዓዊ ድጋፍ ሥራዎች የነቃ ተሳትፎ ማድረጋቸውን በሱዳን የኢፌዲሪ ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ ገልጸዋል፡፡
አምባሳደሩ ይህንን የገለፁት በካርቱም የኢፌዲሪ ኤምባሲ በሱዳን ከሚገኙ የኢትዮጵያውያን ዲያስፖራዎች ጋር የ2013 የበጀት ዓመት የዲያስፖራ ዘርፍ የሥራ አፈጻጸም ሐምሌ 01/2013 ዓ.ም ግምገማ በአደረጉበት ወቅት ነው፡፡
ከዚህ አኳያ ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ 1 ነጥብ 6 ሚሊዮን ብር፣ ለገበታ ለሀገር ፕሮጄክት 1 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር ፣ ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፍ 1 ሚሊዮን ብር ፣ ለኮሮና መከላከያ 779 ሺህ ብር፣ ለሰብዓዊ ድጋፍና መልሶ ማቋቋም ከ217 ሺህ ብር በአጠቃላይ በበጀት ዓመቱ ከ5 ነጥብ 5 ሚሊዮ ብር ከዳያስፖራው መሰብሰቡ ተገልጿል፡፡
ከሀገራዊ ፕሮጄክቶች ተሳትፎ ባሻገር 216 ኢትዮጵያውያን በግላቸውና በማኅበር በመደራጀት በሀገር ቤት በአነስተኛና መካከለኛ ኢንቨስትመንት እና የንግድ ሥራዎች ለመሳተፍ ተደራጅተው ወደ ሀገር እንዲገቡ ድጋፍ ተሰጥቷል፡፡ በተጨማሪም 29 የዳያስፖራ ስብስቦችን ማጠናከር ተችሏል፡፡
በሱዳን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን መብታቸው ተከብሮ እና ጥቅማቸው ተጠብቆ እንዲኖሩና ለሚፈጸምባቸው የመብት ጥሰት የሕግ ከለላ እንዲያገኙ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትኩረት ተሠርቷል ነው የተባለው፡፡
በሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር ወደ ሱዳን ገብተው የታሰሩ 645 ዜጎችን በማስለቀቅ ወደ ሀገራቸው እንዲገቡ ማድረግ እንደተቻለም ተጠቅሷል፡፡
እንዲሁም ከ2 ሺህ 600 በላይ ዜጎች በራሳቸው ትራንስፖርት በመተማ በኩል ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ድጋፍ ተሠጥቷል፡፡
በአሠሪዎቻቸው ደሞዛቸውን የተከለከሉ ዜጎች ጉዳይ ክትትል በማድረግ 181 ሺህ ብር እንዲከፈላቸው ማድረግ መቻሉ እና የአካል ጉዳትና ሞት የደረሳባቸውን ዜጎቻችን 141 ሽህ ብር ካሳ እንዲከፈላቸው ድጋፍ መሰጠቱም ተብራርቷል፡፡
የተለያዩ ችግሮች የደረሰባቸውን ዜጎች ለማቋቋም 51 ሽህ ብር ከኤምባሲው ሠራተኞችና ግለሰቦች በማሰባሰብ ድጋፍ መደረጉም ተገምግሟል፡፡
በመጨረሻም አምባሳደር ይበልጣል አዕምሮ በበጀት ዓመቱ ከዲያስፖራ ጋር በተያያዘ የተከናወኑት ሥራዎች ኤምባሲው ከኢትዮጵያዊያን ዲያስፖራ አባላትና አደረጃጀቶች ጋር በመቀናጀት የተሰሩ መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ የዳያስፖራ አመራር አካላት ጊዜቸውንና ገንዘባቸውን ለማኅበረሰቡ አገልገሎት በማዋል ላበረከቱት አስተዋጽኦ አምባሳደሩ አመስግነዋል፡፡ መረጃው በሱዳን የኢትዮጵያ ኢምባሲ ነው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ