
“በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የአረንጓዴ ዐሻራ መርኃግብር ለቀጣናው ሀገራት አርዓያ የሚሆን ነው” የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ወጣቶች
ባሕር ዳር: ሐምሌ 02/2013 ዓ.ም (አሚኮ)በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው የአረንጓዴ ዐሻራ መርኃግብር ለቀጣናው ሀገራት አርዓያ እንደሚሆን የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት ወጣቶች ተናገሩ።
መርኃግብሩ ዓለምን እያስጨነቀ ላለው የአየር ንብረት ለውጥ የተሻለ አማራጭ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
በአፍሪካ ሕብረት የወጣቶች ሰላም ግንባታ መርኃግብር ዳይሬክተር ዶክተር ሩክስ አኮ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከቴክኖሎጂና የሕዝብ ቁጥር መስፋፋት ጋር ተያይዞ የአየር ንብረት ለውጥ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ተናግረዋል።
የበካይ ጋዝ ልቀት መጨመርም አፋጣኝ መፍትሔ የሚሻው ጉዳይ መሆኑም ጠቅሰዋል።
በዚህ ረገድ ኢትዮጰያ እያከናወነች ያለው የአረንጓዴ ዐሻራ መርኃግብር ለሀገሪቷ ብቻ ሳይሆን ለቀጣናውም ፋይዳው የጎላ ነው ብለዋል።
መርኃግብሩ በአህጉር አቀፍ ደረጃ ሊስፋፋ እንደሚገባ ገልጸዋል።
ዩጋንዳዊ ወጣት ጃኮብ ዬሩ ሀገሩ በአረንጓዴ ልማት ዘርፍ ከኢትዮጵያ የተሻሉ ልምዶችን መውሰድ እንዳለባት አብራርቷል።
ዓለምን እያሰጋ ያለው የአየር ንብረት ለውጥ ችግር በአረንጓዴ ልማት መከላከል ብቸኛው አማራጭ መሆኑንም ጠቅሰው፤ ችግሩን በአፋጣኝ መቅረፍ ካልተቻለ ትውልዱ አስቸጋሪ ሁኔታ የሚጋፈጥ ይሆናል ነው ያሉት።
ችግሩ በማደግ ላይ ባሉ ሀገራት ይበልጥ አሳሳቢ በመሆኑ ከኢትዮጵያ ልምድ መቅሰምና መተግበር እንደሚያስፈልግ ተናግሯል።
የጤናና የምግብ ተደራሽነትን ለማስፋት የአየር ንብረት ለውጥን መከላከል ላይ ትኩረት ተሰጥቶ መሥራት እንዳለበት የተናገረው ደግሞ የሲሼልስ ዜግነት ያለው ወጣት ያኔክ ሚሜ ነው።
የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የአረንጓዴ ልማት ሥራ ወሳኝ መሆኑን ገልጾ፤ በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ እያከናወነችው ያለው ተግባር አድንቋል።
መርኃግብሩም አፍሪካዊ በሆነ አካሄድ የአፍሪካን ችግር የመፍታት ሂደት መሆኑን እንደሚገነዘብም አንስቷል።
ነገር ግን አፍሪካውያን ትልሞቻቸውን እውን ለማድረግ ግጭቶችን ማስቀረት እንዳለባቸውም ተናግሯል።
ኬኒያዊቷ ወጣት ኢቮን ቼጌ አፍሪካውያን ወጣቶች በአነስተኛ ቦታ የአረንጓዴ ልማት ሥራዎችን ማከናወን እንደሚችሉ ገልጻለች።
እያንዳንዱ ሰው የሚኖርብትን አካባቢ ማልማት ከቻለ ሀገር በቀላሉ እንደምትቀየር ገልጻ፤ ከዚህ አንጻር አካባቢያችንን ለጤናና ለኑሮ ምቹ ማድረግ ይጠበቅብናል ነው ያለችው። ኢዜአ እንደዘገበው።
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ