
“በጸጥታው ምክር ቤት ስብሰባ ፍትሐዊ ተጠቃሚነትን ይዛ የቀረበችው ኢትዮጵያ አሸናፊ ሆናለች“ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር
ባሕር ዳር: ሐምሌ 02/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን የሁለተኛ ዙር የውኃ ሙሌት መነሻ በማድርግ በቱኒዚያ በኩል የግብጽና የሱዳን ጥያቄ የቀረበለት የጸጥታው ምክር ቤት ባካሄደው ጉባኤ ጉዳዩ በአፍሪካ ሕብረት ሊታይ እንደሚገባው ውሳኔ ማስተላለፉ ይታወቃል፡፡
ኢትዮጵያዊያንን በመወከል በጉባኤው የተገኙት የውኃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ስለሺ በቀለ (ኢንጅነር) ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ግንባታ በኢትዮጵያውያን ላብ፣ ደም እና ንዋይ እየተገነባ ያለ ግድብ መሆኑን ለጸጥታው ምክር ቤት አስረድተዋል፡፡
ጉባኤውን አስመልክተው ማብራሪያ የሰጡት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ በዕውቀቱ ድረስ (ዶክተር) በጉባኤው ኢትዮጵያ በጠንካራ ልጆቿ ያሸነፈችበት፤ግብጽና ሱዳንም ከሕግ አግባብ ውጭ በየትኛውም መስፈረት ማሸነፍ የማይችሉ መሆናቸውን አምነው የወጡበት ነው ብለዋል፡፡
የጸጥታ ጉዳይን መከታተል የሚገባው የጸጥታው ምክር ቤትም የሕዳሴ ግድብ አደራዳሪ ኾኖ መቅረቡ ስህተት መኾኑን የተናገሩት መምህሩ ጉዳዩ የሚመለከተው የአፍሪካ ሕብረት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ጉዳዩም አፍካዊያን የራሳቸውን ችግር በራሳቸው መፍታት እንደሚችሉ ትልቅ አቅም ይኾናል ነው ያሉት፡፡
ስለ ግድቡ ጠለቅ ያለ ግንዛቤ የሌለው የጸጥታው ምክር ቤት በአደራዳሪነት ቢገባ ኖሮ የግድቡን ሕልውና አደጋ ላይ የሚጥል ውሳኔ ሊወስን እንደሚችልም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ምክር ቤቱ በኢትዮጵያ ጎን የተሰለፉ ሀገራት የሰጡትን የውሳኔ ሐሳብ በማዳመጥ ተገቢ ውሳኔ መወሰኑንም አስገንዝበዋል፡፡
ውሳኔው የአፍሪካ ጉዳይ በአፍሪካዊያን መፈታት አለበት የሚለውን አፍሪካዊ መርህ በተግባር ያስመሰከረ እንደሆነም ነው ያብራሩት፡፡
ኢትዮጵያ እየተደረገ ያለውን የውጭ ጣልቃ ገብነት ለመከላከል ጠንካራ ዲፕሎማቶችን ማፍራትና በሥነ ተግባቦት ዘርፍ ሰፊ ሥራ መሥራት እንዳለባትም ተናግረዋል፡፡
ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ዋጋ እየከፈለች መሆኗን ጠቅሰው መንግሥት በዲፕሎማቶች ላይ የሚሠራውን ሥራ ማጠናከር እንዳለበትም ገልጸዋል።
በስብሰባው ኢትዮጵያ አሸናፊ ኾናለች ያሉት የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህሩ ኢትዮጵያ ይዛ የቀረበችው የመከራከሪያ ሐሳብም ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የሚያሳይና ጠንካራ አስተያዬት የተሰነዘረበት ነው ብለዋል፡፡
በቀጣይም በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የሚገኙ ዲያስፖራዎች፣ የብዙኃን መገናኛ ድርጅቶች፣ ተመራማሪዎችና ሕዝቡ የግብጽን እኩይ ሴራ በማጋለጥ የሕዳሴ ግድብ በሰላም ተጠናቆ ዜጎችን ተጠቃሚ እንዲያደርግ በቁርጠኝነት መሥራት ይገባል ብለዋል፡፡
ዘጋቢ፡- አዳሙ ሽባባው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ