“የጸጥታው ምክር ቤት የህዳሴ ግድብ ጉዳይ በአፍሪካ ሕብረት ይታይ ማለቱ ትልቅ የዲፕሎማሲ ስኬት ነው” የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ

114
“የጸጥታው ምክር ቤት የህዳሴ ግድብ ጉዳይ በአፍሪካ ሕብረት ይታይ ማለቱ ትልቅ የዲፕሎማሲ ስኬት ነው” የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 02/2013 ዓ.ም (አሚኮ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል ዐቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ የሚኒስቴሩን ሳምንታዊ የዲፕሎማሲ ሥራዎችን አሰመልክተው በሰጡት መግለጫ በሳምንቱ የሰሜን የሀገሪቱ ክፍል ያለውን ሁኔታ በተመለከተ ለተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች ማብራሪያ ተሰጥቷል። መንግሥት የወሰነው የተናጥል ተኩስ አቁም ውሳኔ በድንገት ያልሆነና ለብዙ ጊዚያት የተመከረበት እንደሆነና ለውሳኔው ምክንያት የሆኑ ጉዳዮች ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ ግንዛቤ ተፈጥሯል ብለዋል።
በትግራይ በኩል እርዳታ ማድረግ ለሚፈልጉ በጎ አድራጊዎች በአዲስ አበባ በኩል አልፈው እንዲሄዱ የበረራ ፈቃድ መሰጠቱንም ገልጸዋል። ድጋፉን ለማጠናከር በአሸባሪው ሕወሓት የፈረሰውን የተከዜ ድልድል ለመጠገን እየተሞከረ መሆኑንም ተናግረዋል።
በህዳሴ ግድብ ዙሪያ የተፋሰሱን ሀገራት አምባሳደሮች በማግኘት ስኬታማ ውይይት መካሄዱን ጠቁመዋል።
ግብጽና ሱዳን የግድቡን ጉዳይ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት መውሰዳቸውና የአረብ ሊግም የአፍሪካ ሕብረትን በናቀ መንገድ ደብዳቤ መፃፉም የተፋሰሱን ሀገራት እንዳስከፋ አምባሳደሮቹ መግለጻቸውን አስታውቀዋል። ጉዳዩ የልማት እንጅ የጸጥታ ጉዳይ ባለመሆኑ ወደ ጸጥታው ምክር ቤት መሄድ አልነበረበትም፤ ሆኖም የጸጥታው ምክር ቤት ጉዳዩ በአፍሪካ ሕብረት ይታይ ማለቱ ትልቅ የዲፕሎማሲ ስኬት ነውም ብለዋል።
ኢትዮጵያዊያን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መሥሪያ ቤት በመገኘት ላስተላለፉት መልዕክትና ለፈጠሩት ተፅዕኖ ምስጋና አቅርበዋል።
በሳምንቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከደቡብ ኮሪያና ከስዊድን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጋር የስልክ ውይይት አካሂደዋል።
የተናጥል የተኩስ አቁም ውሳኔና የሀገራቱ ግንኙነት የውይይቶቹ አበይት አጀንዳ እንደነበር አመላክተዋል።
የኢትዮጵያ የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮችም በተወከሉበት ሀገር በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ፣ ጸጥታ ሁኔታና በአረንጓዴ ዐሻራ ላይ ስኬታማ ውይይቶች ማካሄዳቸውን ገልጸዋል። በኢኮኖሚው ላይ ባሉ እንቅፋቶችና መፍትሔዎቹ ላይ የሚመክር የኢኮኖሚ ፎረምም ተካሂዷል።
21 ሽህ 182 ዜጎች ወደሀገራቸው ተመልሰዋል ነው ያሉት፡፡
ዘጋቢ፡- ዘመኑ ታደለ – ከአዲስ አበባ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous articleበመዲናዋ የሚኖሩ ባለሀብቶች ለመከላከያ ሠራዊትና ለህዳሴ ግድብ የሚጠበቅባቸውን ድጋፍ እንደሚያበረክቱ አስታወቁ።
Next articleየ6ኛ ሠርዶ ሜካናይዝድ ክፍለ ጦር ለወልዲያ እና ለቆቦ ማኅበረሰብ ምስጋና አቀረበ፡፡