
ፓን አፍሪካኒዝም በትዊተር ዘመቻው
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 02/2013 ዓ.ም (አሚኮ) በኢትዮጵያዊያን ስዓት አቆጣጠር ምሽት 12፡00 ስዓት ጀምሯል፡፡ ኢትዮጵያዊያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች በማኅበራዊ የትስስር ገጽ በተለይም ደግሞ በቲውተር ደምቀው አመሽተዋል፡፡ ፍትህን የሻቱ፣ ጣልቃ ገብነትን የተቃዎሙ እና አፍሪካዊ ነፃነትን ዳግም ለመላበስ የፈለጉ ወጣቶች “እሳት ለብሰው እሳት ጎርሰው ትንታግ ትንታግ” የሆነ መልዕክት ከአራቱም አቅጣጫ ወደ ኒው ዮርክ ይወረወራል፡፡
ኢትዮጵያዊ ጨዋነት እና አፍሪካዊ ትህትና በመልዕክቶቻቸው እንደተጠበቁ ናቸው፡፡ ትዊተር አረንጓዴ ቀለም ዘርቶ፣ ቢጫ ቀለም ጸንሶ ቀይ ቀለም የወለደ ይመስል ዘመን አይሽሬው የአፍሪካዊያን የነፃነት ተምሳሌት እና የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በትዊተር ከፍ ብሎ ሲውለበለብ አመሸ፡፡
የቋንቋውን ብዝኃነት፣ ሐሳቡ የተዘረጋበት አድማስ ስፋት እና የተሳታፊውን ብዛት ላስተዋለ በእርግጥስ ዘመቻው በአንድ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ብቻ ያተኮረ ይሆን? ብሎ እንዲጠይቅ ያስገድዳል፡፡

የፓን አፍሪካኒዝም ድምፆች የበላይነት በወሰዱበት ምሽት የጥንታዊያኑ ሞኖሮቢያ እና ካዛብላንካ ቡድኖች ዛሬ በአንድ ላይ ቆመው “ፍትሕ ለአፍሪካ፣ ፍትህ ለኢትዮጵያ፣ ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ” ሲሉ አመሹ፡፡
የኢትዮጵያ ጠላቶች ከመሬት ተነስተው በአንድ ምሽት ተወልደው ቢያድሩም በዚህ የዘመቻ አውድ ግን ድምፃቸው ተውጦ አመሸ፡፡ በተቃውሞ ከተናጠው የኒው ዮርኩ የጸጥታው ምክር ቤት የመወያያ አጀንዳ ውጭ በትዊተር ብቅ ብቅ የሚሉ ሌሎች የዜሮ ድምር ውጤት ተቃውሞ ድምጾች ሰሚ ጆሮ እና አስተዋይ ልቦና አጡ፡፡
ምሽቱ ከኢትዮጵያ የከፍታ ጉዞ ውጭ ሌሎች ሐሳቦችን ለማስተናገድ የፈቀደም የወደደም አይመስልምና የካይሮ ልዑካን ከሜዳው የወጡት በጊዜ ነበር፡፡
“የሃይማኖት ልዩነት፣ የፖለቲካ እይታ መራራቅ፣ የቋንቋ ብዝኃነት እና የባህል ደርዝ ቢኖረንም እንኳን አንድ ኢትዮጵያዊያን ነን እና የበዛ ጣልቃ ገብነታችሁን እንቃዎማለን” አሉ፡፡

ኒው ዮርክ ከሚገኘው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና መሥሪያ ቤት ፊት ለፊት ከቆሙት የኢትዮጵያ ድምፆች በተጨማሪ ስብሰባው ውስጥ ያሉት ድምፆችም ለኢትዮጵያ የተለዩም የሚከፉም አልነበሩም፡፡ ከኬኒያ እስከ ኖርዌይ፣ ከኮንጎ እስከ ሩሲያ፣ ከአሜሪካ እስከ ቻይና የተሰሙት የተሰብሳቢዎቹ ድምፆች “አፍሪካ ችግሮቿን በራሷ ትፍታ” የሚሉ ማደማደሚያዎችን አሰሙ፡፡
በመጨረሻም ኢትዮጵያዊው ልዑክ ዶክተር ኢንጂነር ስለሽ በቀለ “ኢትዮጵያዊያን ከዓባይ ውኃ የመጠጣት መብት አላቸው ወይ?” የሚል አስተዛዛቢ፣ ታሪካዊ እና የስብሰባውን ፍትሐዊነት ጥያቄ ላይ የሚጥል መልዕክት አስተላልፈው እና ኢትዮጵያዊነትን ከፍ አድርገው ዘጉት፡፡
ለሀገራዊ አንድነት እና ሰላም መናጋት ምክንያት ይሆናል የተባለለት “ማኅበራዊ ሚዲያ” ለታላቅ ሀገራዊ አጀንዳ ድምፅ ኾኖ ማየት ምንኛ ተስፋ ሰጭ ነበር፡፡
በታዘብ አራጋው
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ