
ከቀረበው የአፈር ማዳበሪያ 75 በመቶ ለአርሶ አደሮች መሰራጨቱን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ገለጸ፡፡
ባሕር ዳር: ሐምሌ 02/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አርሶ አደሮች ከሰው ሰራሽ የአፈር ማዳበሪያ በተጨማሪ የተፈጥሮ ማዳበሪያን በመጠቀም ምርታማነትን ማሳደግ በተለይ በዘር ወቅት የሚያከናውኑት ተግባር ነው፡፡
የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የግብርና ግብዓት እና ገጠር ፋይናንስ ተወካይ ዳይሬክተር ሙሽራ ሲሳይ በ2013/14 የምርት ዘመን አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ከ127 ሺህ 700 በላይ ኩንታል ምርጥ ዘር መቅረቡን ገልጸዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ ደግሞ 93 በመቶ መሠራጨቱን ጠቅሰዋል፡፡ ምርጥ ዘር ከማቅረብ ባለፈ በወቅቱ የአፈር ማዳበሪያ ጥቅም ላይ እንዲውል ለማድረግም
ለማቅረብ ከታቀደው 7 ሚሊዮን 32 ሺህ 554 ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ ከ5 ሚሊዮን 696 ሺህ በላይ ኩንታል ማቅረብ መቻሉን ዳይሬክተሩ አስታውቀዋል፡፡
እስከ አሁንም የከረመውን የአፈር ማዳበሪያ ጨምሮ ከ6 ሚሊዮን 548 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያ ለሥርጭት መዘጋጀቱን ዳይሬክተሯ ገልጸውልናል፡፡ ከቀረበው ውስጥ 75 በመቶ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች ተሰራጭቷል፡፡
በተለይም ደግሞ ኤን.ፒ.ኤስ ቦሮን እና ዚንክ ቦሮን ከ90 በመቶ በላይ ቀርቧል ተብሏል፡፡
ይሁን እንጅ የዩሪያ አቅርቦት ዝቅተኛ መኾኑን ነው ዳይሬክተሯ ያነሱት፡፡ በዚህ ዓመት የአፈር ማዳበሪያ መግባት የጀመረው ከታሕሳስ አጋማሽ ጀምሮ ቢኾንም መግባት በጀመረበት መጠን የማሰራጨት ውስንነት እንደነበርም ዳይሬክተሯ አንስተዋል፡፡
የሲውዝ ካናል በመርከብ መዘጋት እና አምራች ሀገራቱ ግብዓቱን በተፈለገው ጊዜ አለማቅረባቸውም የሚፈለገውን የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ ለማቅረብ ችግሮች እንደነበሩም ጠቅሰዋል፡፡
ተጨማሪ የአፈር ማዳበሪያ እስኪገባ ድረስ ያለውን ግብዓት በወቅቱ ለሚዘሩ ሰብሎች እንዲሰራጭ እየተደረገ መኾኑን አንስተዋል፡፡ በተለይም ግጭት ተከስቶባቸው በነበረባቸው አካባቢዎችም ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መኾኑን አንስተዋል፡፡
ምርት እና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚረዱ የተፈጥሮ ማዳበሪያ እንደ ኮምፖስት የመሳሰሉ ግብዓቶችንም አርሶ አደሮች እንዲጠቀሙ ወይዘሮ ሙሽራ አሳስበዋል፡፡
ዘጋቢ፡- ዳግማዊ ተሠራ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ