ʺቢልኩበት ላከ ቢጠሩት እንቢ አለ፣ መውዜሩን በጫንቃው በወገቡ ሽጉጥ እያንከባለለ”

413
ʺቢልኩበት ላከ ቢጠሩት እንቢ አለ፣
መውዜሩን በጫንቃው በወገቡ ሽጉጥ እያንከባለለ”
ባሕር ዳር፡ ሐምሌ 02/2013 ዓ.ም (አሚኮ) አንተ ኩራ ከጀግና ሕዝብ አብራክ የተፈጠርክ፣ ታሪክህን ከተራራ ጫፍ ላይ ያስቀመጥክ፣ ጀግንነትክን በዓለም ስላስመሰከርክ፣ ጠላቶችህን ከወንዝ ማዶ ስለመለስክ፣ እኩይ ሥራ ስላመከንክ፣ ኃያል ነን ያሉትን ስላንበረከክ፡፡ አንተ ኩራ ጦር መጣ ሲሉት ከሚስቅ፣ ሰማይ ተደፋ ምድር ታመሰች ሲባል ከማይጨነቅ፣ ከረገጠበት ወደ ፊት እንጂ ወደኋላ ከማይለቅ፣ የጠላትን ጉሮሮ ለማነቅ ከሚያፍቅ፣ ከድል ላይ ድል እያመጣ ሌላ ድል ከሚናፍቅ፣ በአንድ ድል ከማይረካ፣ የሰው ክብር ከማይነካ፣ ጀግንነቱ ከማይለካ፣ አስተዋጽዖው ከማይተካ ሕዝብ አብራክ ወጥተሃልና አንተ ኩራ፡፡
ጌታህን ፍራ፣ በዘመነህ ክፉ አትስራ፣ ለተቸገረ ራራ፣ ወገንህን አኩራ እንጂ ቀስቅሶ ለገጠምህ፣ በላይ ሆኖ ልርገጥህ ለሚልህ ጊዜ አትስጠው፣ ከትቢቱ አወርደው፣ በፍትሕ መንገድ አስሂደው፤ ከሚል ሕዝብ ተፈጥረሃልና አንተ ኩራ፡፡
ጀግንነትክን፣ ሀገር ወዳድነትክን፣ አርቆ አሳቢነትክን፣ የሀገር ሚዛንነትንክን ወዳጅህ አይደለም ጠላትህ መስክሮልሃል፡፡ የተወለድክበት ምድር፣ የረገጥከው አፈር፣ ያለፍክበት ጎራ፣ የተጠለልክበት ተራራ ሁሉ አፍ አውጥቶ ድንገት ቢያወራ፣ ለምስክር ቢጠራ ጀግንነትክን ሳያጓድል፣ አንዱንም ሳይጥል፣ ሳያናጥብ፣ ነጥብ በነጥብ ይመሰክራል፡፡ የኢትዮጵያ ድንበር በተነካበት፣ ጠላት ብቅ ባለበት ሁሉ የእርሱ ደም ፈስሶበታል፣ የእርሱ አጥንት ተከስክሶበታል፡፡
በራሱ ይተማመናል፣ ወገን ያምናል፣ ጠላትህ ነኝ ብሎ እስኪነሳበት ድረስ ሰውን በጠላትነት አይወነጅልም፣ አይፈርጅም፡፡ በአንዲት ኢትዮጵያ ያምናል፣ በጸና ኢትዮጵያዊነት ይተማመናል፡፡ ክብሩና ማዕረጉ ስለ ኢትዮጵያ መሥራት፣ በኢትዮጵያ መኩራት፣ ስለ ኢትዮጵያ መሟገት፣ ስለ ኢትዮጵያ መሞት ነው፡፡ ከምሥራቅ ንፍቅ፣ እስከ ምዕራብ ንፍቅ፣ ከደቡብ ንፍቅ እስከ ሰሜን ንፍቅ በኢትዮጵያ የሚኖሩ ሁሉ ወንድሞቹ፣ እህቶቹ፣ አብሮ አደግ ጓደኞቹ እንደሆኑ ያምናል፡፡ አብሯቸው ይኖራል፣ አብሯቸው ይሞታል፡፡ ከሁሉም ኢትዮጵያን ጋር በኢትዮጵያዊነት ጥላ ሥር፣ በፍቅር እንኑር ይላል አማራ፡፡
ኢትዮጵያ የጋራ ቤት፣ የጋራ እርስት፣ የጋራ እናት ናት ይላል፡፡ ሀገር አይሸጥም፣ ከኢትዮጵያዊነት ጸባዩ አይለወጥም፣ ከአንድነት መንገድ አያፈነግጥም፣ ወገኑን በምንም አይለውጥም፡፡ ከእኔ በፊት አንተ አጊጥ፣ ከእኔ በፊት አንተ ብላ፣ አንተ ከምትሞት እኔ ልሙት ይላል፡፡ ክፉ አይናገር፣ ሀሰት አይመሰክር፣ ግርማው አይደፈር፣ ለፈተና አይበገር፡፡ አማራ በሠዓቱ ጸሎት ያደርሳል፣ በወራቱ አደባልቆ ያርሳል፣ አጣርቶ ከሰፊ አውድማ ላይ ያፍሳል፣ ሳይሰስት ያጎርሳል፣ በጠጅ በጠላ፣ በማር በጮማ አንጄት ያርሳል፣ የተበደለን እንባ ያብሳል፣ የታረዘን ገላ በክብር ያለብሳል፣ አልሞ ይተኩሳል፣ ለይቶ ይበጥሳል፡፡
ʺከመውጫ መውረጃው ቤት ሠርቷል ከመንገድ፣
ወይ ማብላት ማጠጣት ወይ እንግዳ መውደድ” እንደተባለ እንግዳ ሲቀበል፣ ከቤት እግብቶ ሲያቀማጥል፣ ጨማ እየቆረጠ፣ ጤፍ እንጀራ በእርጎ ያጎርሳል፡፡ ጠላ በዋንጫ ጠጅ በብርሌ ያጠጣል፡፡
ከእንግድነት አልፎ ባላንጣ ሆኖ ለመጣው ደግሞ፤
ʺአዎይ አተኳኮስ ወይ ደፋር መሆን፣
ሲሄድ መቀነቻ ሲዞር ግንባሩን ” እንደተባ መቀመጫ ወንበር ባዘጋጄበት፣ ጤፍ እንጀራ ባጎረሰበት፣ ጮማ በቆረጠበት፣ ጠጅ በቀዳበት እጁ ይተኩሳል፤ ከድንበር ማዶ ይመልሳል፡፡
አማራ ታግሶ ጠላቱን ሲያጠቃ ከቻልክ ግንባሩን፣ ካበለዚያ እግሩን በለው ይላል፡፡ ወዳጅህን አጉርስ፣ ጠላትህን ታገስ፣ ምከረው ዝከረው፣ እንቢ ካለ ክንድህን አሳዬው መገለጫው ነው፡፡ ሀገር ስትነካ ሲነሳ፣ ወገን ሲደፈር ሲያገሳ፣ ወዮለት ለዚያ ጠላት ነብሱን ለቀይ ጥይት አሳልፎ ለሰጣት፣ ከማይገፋ ተራራ ጋር ላጋጠማት፣ ከሚውጥ ውቂያኖስ ለወረወራት፣ ለፈርጣማ አንበሳ ላቀበላት፡፡
አማራን የሚጠሉት፣ ማሸነፍን የሚመኙት፣ መጣንብህ ይሉታል፣ እንኳን መጣንብህ ተብሎ መጥተውበትም ልቡ አይሸበር፣ በጀግንነቱ አይጠረጠር፡፡
ከሁሉም ፍቅር ይሻላል፣ መከባበር ዘመን ያሻግራል፣ ሰላም ፍሬ ያፈራል፣ ጸብ ግን ያከስራል ይላል፡፡ ይህን ሁሉ አልፈው፣ ድንበር ዘለው፣ አጉራ ነቅለው ከመጡ ግን፣ በአረሰና በአጎረሰ እጁ ይተኩሳል፣ ከሞፈሩ ግርጌ በክብር ያስቀመጠውን ነፍጥ ያነሳል፣ አማራ ሀገሩና ክበሩ ከነተካ፣ ጥይትና ጠመንጃው ከተሰካካ ላይመለስ ይዘምታል፡፡ ጠላትን ከወዳጁ እየለየ ይመታል፡፡
የጣልያን ሠራዊት ያልበገረውን፣ በሰማይ የተጣለ ቦንብ ያላስደነገጠውን፣ የጠላት ውሽንፍር ያልመለሰውን ጀግና ሕዝብ መጣንብህ ይሉታል፡፡ የመጡበት ለወሬ ነጋሪ ሳይመለሱ ሲቀሩ፣ የጀግኖች ሳንጃ ሲበላቸው፣ እንደ ገሞራ የሚናደፈው ግርማው ሲያቃጥላቸው፣ እንደ ቆሎ ሲጨብጣቸው እያዬ መጣንብህ ይሉታል፡፡
ለእንግዳ ወተት፣ ለጠላት ጥይት ሳይዝ ይቀመጥ ይመስል፡፡
ከሚወደው ሕዝብ ስለወጡ፣ ከሚወዳት ሀገሩ አብራክ ስለመጡ፣ አምኗቸው ሀገር ምሩ፣ ታሪክ ሠሩ፣ የቀደመውን ዘክሩ፣ ሕዝብን በጥበብ አሻግሩ አላቸው፡፡ እነርሱ ግን ሲያምናቸው ከዱት፣ ሲያጎርሳቸው ነከሱት፣ ጥላ ከለላ ሲሆናቸው ገደሉት፣ ከቤቱ ሲያሳርፋቸው ከድካም ማረፍ ሲገባቸው፣ አመስግነው ማለፍ ሲጠበቅባቸው ከቤትህ ውጣ፣ ንብረትህን አምጣ አሉት፡፡ መንገድ እየመራ አምኖ ሲያስከትላቸው ከኋላው ገደሉት፡፡ ከሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጋር አምኖ የሰጣቸውን ሀገሩን ከዷት፡፡ ጠብተው አድገው ጉልበት ሲያገኙ፣ ለበቀል ሲደርሱ አጥብታ ያሳደገችን እናት ጡቷን ነከሷት፡፡
እርሱም መካዳቱ ሲገባው፣ የሀገሩ ክብር ዝቅ ማለት ሲያንገበገብው፣ ከቀደሙት በቀደመች፣ ከዘመኑት በዘመነች፣ በጨለማ ዘመን መርታ ባሻገረች፣ ለምስክር፣ ለክብር፣ ለዓለም ምሥጢር መፍቻ ቁልፍ በሆነች ሀገር ተከባብረው፣ ተዋደው፣ እንደ ፈትል ተጋምደው፣ እንደ ችቦ በጋራ ነደው በኖሩባት ሀገር ክልል ከልሎ፣ ወሰን አበጅቶ፣ መለያያ አዘጋጅቶ የፍቅሯን ቤት፣ የጠብ መዶለቻ ሲያደርጓት ተው ይህ ነገር አይሆንም አለ፡፡ ሲታመኑ መክዳት፣ በሚያልፍ ዘመን የማያልፍ ግፍ መሥራት፣ ለሀገር የኖረን፣ ከበረሃ አውጥቶ ወግ ማዕረግ ያሳዬን፣ ከመደብ አንስቶ ዙፋን ላይ ያስቀመጠን ሕዝብ ጠላት ማለት ግፍ ያመጣል፤ ቁጭ ብላችሁ የሰቀላችሁት ቆማችሁ ለማውረድ ትቸገራላችሁ ተው አይበጅም አላቸው፡፡
በለስላሳ አንደበቱ፣ አርቆ በሚያስበው ብልህነቱ፤ ተው ይህ ነገር አይበጅም በመልካም ሕዝብ ስም አትነግዱ፣ በሕዝብ ስም እየተጓዛችሁ በራስ መንገድ አትሂዱ፣ ከፍ ያለን ታሪክ አታዋርዱ አላቸው፡፡ አልሰሙትም፣ ይባስ ብለው አሠሩት፣ ገደሉት፣ አሳደዱት፡፡ ምን አልባትም ልብ ይሰጣቸው ይሆናል በሚል ተስፋ በትዕግስት ዝም አላቸው፣ ከደደቢት በረሃ እስከ ቤተ መንግሥት፣ የአማራን ገበሬ ከፊት አሰልፎ መንገድ እያስጠረገ ዙፋን ላይ የተቀመጠው ወያኔ መካስ ሲገባው ወቀሰው፣ ማጉረስ ሲገባው ነከሰው፡፡ ግፉ በዛ፣ መከራው ጸና ትዕግስት እያለቀ ሄደ፡፡
አማራ በደል እየበዛበት፣ ጥላቻ እየተዘራበት፣ መከራው እየጸናበትም በዳዬ ቡድን እንጂ ሕዝብ አይደለም ይላል፡፡ ተቻኩሎ አይፈርድምና ስለ ትግራይ ሕዝብ ያለፈው ፍቅርና ክብር አንድም ቀን አይቀንስም፡፡
የግፍ ዘመን አልቆ የትህነግ ዘመን ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያ የምትኮራበትን፣ ኢትዮጵያዊያን የሚመኩበትን ነካ፡፡ ከመነሻው ጀምሮ ጠላቴ ያለውንም ተነኮሰ ያን ጊዜ ፍጻሜ ዘመኑ ደረሰ፡፡ መርቶ ያመጣው ሕዝብ፣ አባሮ ዋሻ ውስጥ አስገባው፡፡ ከዋሻ ውስጥ ገብቶም ክፋቱን አልተወም፣ የዘረፈውን ሮኬት ወደ አማራ ሕዝብ ወረወረ፡፡
ይባስ ብሎ የማይካድረው የዘር ፍጅት፣ የዘመናት የወልቃት፣ የራያ ስቃይና ሞት ሳይረሳ፣ ደሙ ሳይደርቅ፣ ሀዘኑ ሳይለቅ፣ ጥቁሩ ልብስ ሳይወልቅ ʺአወራርድብሃለሁ” ይል ጀምሯል አሸባሪው ትህነግ፡፡ አማራ ድሮ በመራበት ጥይቱ፣ ማዕበል በማያናውጠው ጀግንነቱ አሳፍሮ እንደሚደመስሰው፣ አፈር እንደሚያለብሰው አላወቀምና፡፡ ʺቢልኩበት ላከ ቢጠሩት እንቢ አለ፣
መውዜሩን በጫንቃው በወገቡ ሽጉጥ እያንከባለለ” እንዳለ ዘፋኙ አማራ ከመጣህ ለፍቅር እጃችን፣ ለጥል ደግሞ አፈሙዛችን ተዘጋጅቷል እያለው ነው፡፡ እንደ አመጣጡ ለመመለስ መውዜሩን እያንከባለለ፣ በአንድ እጁ መልካሙን መሬት እያረሰና እያለሰለሰ ተቀምጧል፡፡ ከነብሱ አስበልጦ የሚወዳትን፣ ደጋግሞ የሚጠራትን፣ አክብሮ የሚኖርላትን ሀገሩን ለመውጋት ለተዘጋጄው የውጭ ጠላትም ዝግጁ ነው፡፡
አማራ መጣውብህ ተብሎ አይፈራም፤ ለመጡበትም አይራራም፡፡ አዎ አንተ ኩራ ጀግና ነሕና፡፡ በዳር ቢዞሩ፣ በጎረቤት ቢያስወሩ ሁሉም ከጀግንነትህ በታች ናቸው፡፡ እንኳን እየነገሩህ ሳይነግሩህ መጥተውም እንዳልቻሉህ አትዘንጋ፡፡ ዳር ዳር የሚዞሩህ ስለሚፈሩህ ነው፡፡
በታርቆ ክንዴ
ተጨማሪ መረጃዎችን ከአሚኮ የተለያዩ የመረጃ መረቦች ቀጣዮቹን ሊንኮች በመጫን ማግኘት ትችላላችሁ፡፡
በዌብሳይት amharaweb.com
በቴሌግራም https://bit.ly/2wdQpiZ
Previous article“የአሸባሪው ትህነግ በደልና ሴራ የአማራን ሥነልቦና አጠነከረው እንጂ አላዳከመውም”
Next articleከ250 ዓመታት በፊት የታተመ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ ለባሕል እና ቱሪዝም ሚኒስቴር ተበረከተ፡፡